የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በከተማው እየሠራ የሚገኘው አዳማ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡
ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በአዲሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በጥምረት በማቀፍ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በክለቡ መቀመጫ በሆነች አዳማ እየከወነ የሚገኘው አዳማ ከተማ የመስመር ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን እና አጥቂው አብዲሳ ጀማልን ውል ለተጨማሪ ዓመት ሲያድስ የጊኒ ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂ ሴኩምባ ካማራን ውል ለማደስም በሂደት ላይ መሆኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
የመስመር ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ለሁለት ተጨማሪ አመት በአዳማ ከተማ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡ ይህ የቀድሞው የሀምበሪቾ ዱራሜ፣ አዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም የሲዳማ ቡና ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር አመት እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በጉዳት ካጋመሰ በኋላ ነበር የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ጥሪ ተቀብሎ በመጋቢት ወር አዳማን የተቀላቀለው። ተጫዋቹም ለክለቡ የአንድ አመት ውል ፈርሞ የነበረ ሲሆን ስድስት ወራትን በጥሩ ብቃት ክለቡን በማገልገሉ ቀሪ የስድስት ወራት ቢቀሩትም ተጨማሪ ሁለት ዓመት በክለቡ ለመዝለቅ ፈርሟል፡፡
ሌላኛው ውሉን ያራዘመው አጥቂው አብዲሳ ጀማል ሆኗል። ሻሸመኔ ከተማን ከለቀቀ በኋላ በመጀመሪያው ዓመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በአዳማ ከተማ መለያ መልካም ጊዜ አሳልፏል፡፡ በጉዳት ካመለጡት ጥቂት ጨዋታዎች ውጪ ለክለቡ በመሰለፍ በዓመቱ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ይህ ፈጣን አጥቂ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ከአዳማ ጋር ቢኖረውም እስከ 2015 በክለቡ ቆይታ ለማድረግ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውሉን አድሷል፡፡