አርባምንጭ ከተማ ኬንያዊ ተከላካይ አስፈረመ

አዞዎቹ በባህር ዳር ተዘጋጅቶ በነበረው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ለኬንያ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የነበረውን ተከላካይ አስፈርመዋል፡፡

ከሦስት አመታት በኋላ በድጋሚ የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ አሸናፊ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በከተማው አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማቀፍ መስራት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ቀደም ብሎ ከሀገር ውስጥ ክለቦች ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ቡድኑ አሁን ደግሞ ስድስተኛ ተጫዋች በማድረግ ኬንያዊው በርናርድ ኦቼንግን ማስፈረሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

የመሐል ተከላካዩ በርናንድ ኦቼንግ አብዛኛው የእግርኳስ ህይወቱን በሀገሩ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ በሆነው ቪሂጋ ዩናይትድ ያሳለፈ ሲሆን ያለፉትን አራት ዓመታትም ለኬንያ ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ በባህርዳር ተዘጋጅቶ በነበረው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ሀገሩ ኬንያን ወክሎ ሲጫወት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በስፍራው ተገኝተው ከተመለከቱት በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አዞዎቹን ሊቀላቀል ችሏል፡፡