የቡናማዎቹ የመስመር ተጫዋች ከእሁዱ ወሳኝ ጨዋታ ውጪ ሆኗል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ የዩጋንዳውን ዩ አር ኤ የሚገጥመው ኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂውን ግልጋሎት እሁድ እንደማያገኝ ታውቋል።

ባሳለፍነው እሁድ ወደ ዩጋንዳ አምርተው በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ዩ አር ኤ’ን ገጥመው 2-1 ተሸንፈው የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ቋሚ ሆኖ ወደ ሜዳ የገባውን የመስመር አጥቂ ሚኪያስ መኮንንን በጉዳት ምክንያት ቀይረው ማሶጣታቸው ይታወሳል። እሁድ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ ለማድረግ በነገው ዕለት ወደ ስፍራው የሚያመራው ቡድኑም ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ያላገገመውን ተጫዋች እንደማይጠቀምበት ተረጋግጧል።

በሴንት ሜሪ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በ38ኛው ደቂቃ ጉልበቱ ላይ ግጭት አጋጥሞት ተጎድቶ በአላዛር ሽመልስ ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደው የመስመር አጥቂውም በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ሁኔታ እያገገመ ቢሆንም ለእሁዱ ወሳኝ ጨዋታ ግን እንደማይደርስ ታውቋል።

ያጋሩ