የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ ከአል ሂላል ጋር የሚያደርገዋል ፋሲል ከነማ ነገ ወደ ስፍራው ጉዞውን ያደርጋል።
በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመሩ የሊጉን ዋንጫ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍ አድርገው ያነሱት ፋሲል ከነማዎች በአህጉራዊው ትልቁ የክለቦች የውድድር መድረክ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። ክለቡም በመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር ተደልድሎ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ 2 አቻ ተለያይቷል።
የፊታችን እሁድ ደግሞ የመልሱ ጨዋታ የሚጠብቀው ክለቡ በዛሬው ዕለት ባህር ዳር ላይ ሲሰራ የነበረውን ልምምድ አገባዶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ታውቋል። ከሰዓታት በፊት ሶከር ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚያመሩ ተጫዋቾችን ዝርዝር ይፋ ያደረገች መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይ ሀያዎቹን ተጫዋቾች ጨምሮ 32 አባላት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ አረጋግጠናል።
ነገ 5 ሰዓት ወደ ሱዳን የሚያመራው የክለቡ የልዑካን ቡድንም ዛሬ ከሰዓት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አዳሩን በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አድርጓል።