ከፊቱ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ያሉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በቀጣይ ሳምንት ዝግጅቱን ይጀምራል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ በተመሳሳይ 1-0 ውጤት ሽንፈት እና ድል አስተናግዷል።
የምድብ ሦሰተኛ እና አራተኛ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ ጋር በተከታታይ በሜዳው መስከረም 26 እና ከሜዳው ውጪ መስከረም 30 የሚያደርገው ቡድኑም ለተጫዋቾች ጥሪ ሊያቀርብ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ለደቡብ አፍሪካው የደርሶ መልስ ጨዋታም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ እንደሚተላለፍ የሰማን ሲሆን የተጫዋቾቹ ስም ዝርዝርም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ጥሪ የሚደርሳቸው ተጫዋቾች ከአራት ቀናት በኋላ (መስከረም 12) ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚደረግ ሲሆን በማግስቱም መደበኛ ልምምዳቸውን ወደ ባህር ዳር በማቅናት እንደሚከውኑ ተመላክቷል።