የዐፄዎቹ የግብ ዘብ ሚኬል ሳማኪ ስለ ነገው ጨዋታ ይናገራል

👉”በሜዳችን ያደረግነው ጨዋታ ላይ ያገኘነው ውጤት አርኪ አይደለም”

👉”በዚህ የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ሁላችንም ትኩረታችን አንድ ነገር ላይ ነው። እሱም…”

👉”ለማሸነፍ እና ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ጉጉት ላይ ነን። እንዳልኩት እናደርገዋለን ፤ በቡድኔ ላይም ዕምነት አለኝ”

👉”ሦስት ነጥብ ብቻ ብለን ለማሸነፍ ነው ወደ ሱዳን የሄድነው እንጂ ሀገር ለመጎብኘት አይደለም”

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማ የሊጉ የበላይ በመሆኑ በአህጉሩ ትልቁ የክለቦች ውድድር (አፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ) ላይ የመሳተፍን ዕድል እንዳገኘ ይታወቃል። ክለቡም በዋናው ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ከሳምንታት በፊት በወጣው ድልድልም ክለቡ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር የተደለደለ ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታውንም በሜዳው በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አድርጎ ሁለት አቻ ተለያይቷል። ለመልሱ ጨዋታ በትናንትናው ዕለት ወደ ሱዳን ያቀናው ስብስቡም ወሳኙን የመልስ ጨዋታ በነገው ዕለት ከምሽቱ 12 ሰዓት የሚያከናውን ይሆናል። ከጨዋታው በፊትም የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ ነጥብ የተጋሩበትን እንዲሁም የነገውን ፍልሚያ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

በሜዳችሁ ሁለት አቻ የተለያያችሁበትን ውጤት እንዴት ትገልፀዋለህ?

“በሜዳችን ያደረግነው ጨዋታ ላይ ያገኘነው ውጤት አርኪ አይደለም። ምክንያቱም በሜዳችን ሁለት ጎሎችን ስላስተናገድን። ይህ ደግሞ የመልሱን ጨዋታ ከባድ ያደርግብናል። አል ሂላል በአፍሪካ ከሚገኙ ጠንካራ ክለቦች አንዱ ነው። በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ሲሳተፍም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ጥሩ ልምድ ያለው ክለብ ነው። እንዳልኩት ውጤቱ አመርቂ አይደለም። በጨዋታው የሰራናቸውን ስህተቶች ማረም ይኖርብናል። በተለይ ሌላ ጎል ነገ ማስተናገድ የለብንም።”

ውጤቱ አመርቂ አይደለም ካልከኝ የጨዋታው ልዩነት ምንድን ነበር?

“በዛ ጨዋታ የነበረው ልዩነት የልምድ ብቻ ነው። አል ሂላል ትልቅ ክለብ እንደሆነ በደንብ አሳይተውናል። ከዚህም በተጨማሪ ከእኛ የበለጠ ልምድ እንዳላቸው እና በውድድሩ እንዴት መጫወት እንደሚገባ አሳይተውናል። ቡድኑ በጨዋታው ሁለት እና ሦስት አጋጣሚ ብቻ ነበር ያገኘው። ግን እነዛን አጋጣሚዎች ተጠቀመበት። ውጤቱ ለእኛ አይገባንም ነበር። በጨዋታው በደንብ ጫና ፈጥረን ተጫውተን ነበር። ኳሱንም በሚገባ ስንቀባበለው ነበር። ግን በዚህ ትልቅ ውድድር ላይ ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ስል መሆን ያስፈልጋል። የሚገኙ አጋጣሚዎችን በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የጨዋታው ልዩነት የልምድ ጉዳይ ነው።”

በጨዋታው ቡድናችሁ የጎደለው ነገር ምንድን ነበር?

“እንዳልኩት ልዩነቱ የልምድ ጉዳይ ነው። እኛ ጥሩ ለመጫወት ፈልገን ነበር። ግን በትልቅ የውድድር መድረክ ይህ በቂ አይደለም። ጎሎች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ 10 አጋጣሚዎች ቢፈጠቱ 7ቱን ማስቆጠር ያስፈልጋል። በጨዋታው ጥሩ አጋጣሚዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ አግኝተን ነበር። ግን መጠቀም አልቻልንም። እነሱ ግን ያገኙትን ተጠቀሙ። ይህ እግርኳስ ነወ። አንተ እንደምትስተው ተጋጣሚም አጋጣሚ ላያመክን ይችላል። በአጠቃላይ በሜዳችን ባደረግነው ጨዋታ ጎሉን ዓላማ እንዳደረገ ቡድን አልተጫወትንም ነበር። በሜዳችን እንደመጫወታችን ጎሎችን ማስቆጠር ነበረብን። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ። ይህ ቢሆን ደግሞ ጨዋታው ይቀለን ነበር። ግን ሞክረን አልተሳካልንም። ውጤቱን እንደዚህ የሆነው በመጀመሪያው አጋማሽ ጎሎችን አግብተን ጨዋታውን ባለማቅለላችን ነው።”

ቡድናችሁን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች ስብስባችሁን አጠናክረዋል? ስለእነሱ የሆነ ነገር በለን እስኪ?

“ቡድናችንን ስለተቀላቀሉት አዳዲስ ተጫዋቾች አሁን ምንም ማለት ይከብዳል። ምክንያቱን ገና አንድ ጨዋታ ብቻ ከእኛ ጋር ስላደረጉ። ስለዚህ ማንንም እንዲህ ነው ማለት ይከብዳል። ግን እንደሚታወቀው ፋሲል ከነማ እንደ ሁሌው ጠንካራ ቡድን ነው። ይሄንን ደግሞ አዲሶቹ ተጫዋች የሚረዱ ይመስለኛል። ስለዚህ የሚጠብቃቸውን ስራ የሚያውቁት ይመስለኛል። ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ያላቸውን አቅም 100% አውጥተው ለክለቡ መስጠት ይገባቸዋል። ክለቡም ሆነ ነባር ተጫዋቾቹም ከእነሱ የምንፈልገው ይሄንን ነው። በአጠቃላይ ወደ ጠንካራ ክለብ ስትመጣ አንተም መጠንከር አለብህ።”

ለመልሱ ጨዋታ ልምምዳችሁ እንዴት ነበር?

“ልምምዳችን በጣም ጥሩ ነበር። ሁላችንም ካለፈው ጨዋታ ስህተቶች ትምህርት ወስደናል። በልምምዶቻችን ላይም ለማረም ሞክረናል። ቡድናችን ውስጥም ምንም የጉዳት ዜና አለመኖሩ የሚያስደስት ነው። እናደርገዋለን ብዬ አስባለሁ ፤ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው። ተጫዋቾቹም ጥሩ መነሳሳት ላይ ናቸው። ለማሸነፍ እና ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ጉጉት ላይ ናቸው። እንዳልኩት እናደርገዋለን በቡድኔ ላይም ዕምነት አለኝ።”

በውድድሩ ያላችሁ ዓላማ ምንድን ነው?

“በዚህ የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ሁላችንም ትኩረታችን አንድ ነገር ላይ ነው። እሱም ወደ ምድብ ድልድሉ መግባት ነው። ይህ ቀዳሚው አላማችን ነው። ቀጣዩን ደግሞ በሂደት የምናየው ነው። እናደርገዋለን ብዬ አስባለሁ እንደምታስታውሱት በሁለተኛው አጋማሽ ቡድናችን ለማሸነፍ ፍላጎት አሳይቶ ነበር። አሁንም ሱዳን ላይ ሦስት ነጥቡን ማሳካት እንደምንችል ዕምነቴ ነው። ይህን ደረጃ አልፈን ወደ ምድቡ መድረስም ዋነኛው አላማችን ነው።”

ለነገው ጨዋታ ያላችሁ ዝግጁነት ምን ይመስላል? በግልህስ ምን ያህል ተዘጋጅተካል?

“ለነገው ጨዋታ መቶ በመቶ ተዘጋጅተናል። መቶ በመቶም በግሌ ተነሳሽነቱ አለኝ። እንደምታውቁት በአፍሪካ ትልልቅ ውድድሮች ላይ ተጫውቻለሁ። ከማሊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፌያለሁ ፤ በዋናው እና ከ23 ዓመት በታች። የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከፋሲል ጋር በካፍ ውድድር ተጫውቻለሁ። አሁን ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊጉ ከፋሲል ጋር ተገኝቻለሁ። ስለዚህም እዚሁ መቅረት ሳይሆን የምድብ ጨዋታዎችን ማድረግ ነው ሀሳቤ። ይህ እንዲሆንም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለብኝ። ለዚህም መቶ በመቶ ተነሳሽነቱ አለኝ። ስለዚህ በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ሌላ ታሪክ ለመጨመር ለቡድኔ ፋሲል ከነማ እና ለኢትዮጵያ ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነኝ። እኔ እንዳለኝ መረጃ ከዚህ ቀደም ወደ ምድብ ድልድሉ የደረሰ ቡድን የለም። ስለዚህ አሁን ለምን አናደርገውም ? ሁሉም ነገር አለን ፤ ድንቅ ደጋፊዎች አሉን። ቡድኑም ጥሩ መነሳሳት ላይ ነው ያለው። ስለዚህ እንደምናደርገው ነው የማስበው።”

ስለዚህ ከነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

“ለነገው ጨዋታ የምንሄደው ለማሸነፍ ብቻ ነው። ሜዳ ላይ ምንም ቢፈጠር ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው። ሦስት ነጥብ ብቻ ብለን ለማሸነፍ ነው ወደ ሱዳን የተጓዝነው እንጂ ሀገር ለመጎብኘት አይደለም። ይህንን ነው በእሁዱ ጨዋታ የምንጠብቀው። የእኔም ዕምነት ይኸው ነው።”

ያጋሩ