የአዲስ አበባ ስታዲየምን በባለቤትነት የሚመራው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ለስታዲየሙ እየተደረገ ያለውን እድሳት በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጥቷል።
በብቸኝነት ዘለግ ላሉ ዓመታት ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍ እና ፊፋ የተቀመጠውን መመዘኛ ባለማሟላቱ ከጨዋታዎች መታገዱ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ስታዲየሙን ለጨዋታዎች ለማብቃት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጨረታ በማውጣት በሁለት ዙሮች የእድሳት ሥራዎች እንዲሰሩ አድርጓል። ከዚህም መነሻነት ከወራት በፊት ኮሚሽኑ በ39,644,748.93 የጨረታ ገንዘብ ሥራዎች እንዲጀመሩ አድርጓል። በዛሬው ዕለትም የኮሚሽኑ አመራሮች ባሉበት የስታዲየሙ አሁናዊ ሁኔታ በጋዜጠኞች ምልከታ ተደርጎበታል።
1:35 ደቂቃዎች ዘግይቶ በተካሄደው የቅኝት መርሐ-ግብር ላይ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ እና የተለያዩ ክልል ኮሚሽነሮች በተገኙበት ምልከታ ተደርጓል። በምልከታውም በመጀመሪያ ምዕራፍ የተሰራው የተጫዋች እና የዳኞች የመልበሻ ክፍሎች፣ የኳስ አቀባዮች ማረፊያ እና አጠቃላይ የውስጥ ኮሪደር ሥራዎች እየተገባደዱ እንደሆነ ታይቷል። ምንም እንኳን የመጫወቻ ሜዳው ቁፎሮ ተከናውኖ እንደ አዲስ ሙሌት ተደርጎለት ሥራዎቹ ቢቆሙም ኮሚሽነሩን ጨምሮ በስፍራው የተገኙት አመራሮች ምልከታ አድርገዋል።
አመራሮቹ የግንባታውን ሂደት ከተመለከቱ በኋላ ደግሞ ስለ አጠቃላይ የስታዲየሙ የግንባታ እና አሁናዊ ሁኔታ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውንም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነት አቶ ዱቤ ጅሎ፣ የኮሚሽኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው እና ዮሐንስ ዓባይ አማካሪ ድርጅት ተወካይ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አቶ ዱቤ ጅሎ አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ዱቤ በቅድሚያም ከክልሎች ጋር በሌላ ስፖርቱን በተመለከተ ውይይት ምክንያት አርፍደው በመምጣታቸው ይቅርታ ጠይቀው “የኢፌዴሪ የስፖርት ኮሚሽን በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። በተለይ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በተመለከተ ባሳለፍነው ዓመት ብዙ ስራዎች ሰርተናል። ከምንም በላይ ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ስታዲየሞችን እየሰራን ነው። እንደምታውቁት ሀገራችን ዓለማቀፍ ስታዲየም የሚያደርግበት ሜዳ የባህር ዳር ስታዲየም ብቻ ነው። እሱም መስተካከል ያሉባቸው ጉዳዮች እንዳሉት ካፍ እየነገረን ነው።
“የአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ላለፉት 50 ዓመታት ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎችን የምናደርግበትን ስታዲየም ነበር። ነገርግን ካፍ እና ፊፋ ስታዲየሙ ያለበት ደረጃ ብቁ አይደለም በሚል ከውድድር አግደውታል። እኛም በካፍ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ለማደስ ተንቀሳቅሰናል። በዋናነት ደግሞ የመልበሻ ክፍሎች እና የመጫወቻ ሜዳው ላይ ትኩረት ተደርጎ ከደጋፊዎች መቀመጫ ጋር ሥራዎች እየተሰሩ ነው።” ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ንግግራቸውን ቀጥለው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት እስከ የካቲት አልያም መጋቢት ድረስ ተገባዶ ወደ ግልጋሎት እንደሚገባ ገልፀው በፌደራል ደረጃ እየተሰሩ የሚገኙ ሌሎች ስታዲየሞችን በተመለገተ ተከታዩን ብለዋል።
“ብሔራዊ ስታዲየማችን በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ይገኛል። ይህ የአዲስ አበባ ስታዲየም በተቀመጠው መንገድ አስተካክለን ወደ ግልጋሎት እንዲገባ እናደርጋለን። ጎን ለጎን የባህር ዳር እና የሀዋሳ ስታዲየምም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እየተሰሩ ነው። ከእነዚህ ዋናዎቹ ስታዲየሞች በተጨማሪ ከክልሎች ጋር የምንሰራቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች አሉ። እነዚህም ለወጣቶች እና ታዳጊዎች በቂ የመጫወቻ ስፍራዎች እንዲኖሩ ያደርጋል። በአጠቃላይ በሚቀጥሉት 2 እና 3 ዓመታት ከ3 በላይ ዓልመ አቀፋዊ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች እንዲኖረን እየሰራን ነው።”
ከምክትል ኮሚሽነሩ ሀሳብ በኋላ ደግሞ የአዲስ አበባ ስታዲየም የግንባታ አማካሪ የስታዲየሙን ግንባታ በተመለከተ ገለፃ ማድረግ ይዘዋል።
“ኮንትራቱን የወሰድነው ለአንድ ዓመት ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ካፍ ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሰረት የመልበሻ ክፍሎቹን ማስተካከለደ እና ሜዳውን የማደስ ስራ በዋናነት እየሰራን ነው። ሥራውን በወቅቱ ለመጨረስ እንሞክራለን። ግን በዚህ ሰዓት 14.6 % ያለውን የግንባታ ሒደት ለማጠናቀቅ አስበን 11.6% አሳክተናል። ይህንን ሥራ ሐምሌ 16 በይፋ የጀመርን ሲሆን እስካሁን 57 የስረሰ ቀናትን አሳልፈናል። እንዳልኩትም ሥራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ እየሰራን እንገኛለን።
የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አስመራ በበኩላቸው ኮሚሽናቸው በማዘውተሪያ ስፍራዎች ዙሪያ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሆነ አውስተው የአዲስ አበባ ስታዲየምም በተቀመጠው ጊዜ እድሳቱ እንደሚገባደድ ተናግረዋል።
“የስፖርት ኮሚሽናችን የሪፎርም ስራዎችን እንደሰራ ይታወቃል። በዚህ ሪፎርም ደግሞ በሀገራችን እየተሰሩ ያሉትን ስታዲየሞች ገምግመን ስታንዳርዳቸውን እንዳልጠበቁ አይተናል። ይህንንም አጥንተን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞችን ለመስራት እየሰራን ነው። በዚህም የባህር ዳር ስታዲየም የሜዳ ችግር እንደሌለበት ካፍ ነግሮናል። ስታዲየሙ የመልበሻ ክፍል፣ የፍለድ ላይት እና የተመልካቾች መፀዳጃ ቤት ላይ በዋናነት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውም አስተያየት ተሰጥቶናል። የሀዋሳ እና የአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ከመልበሻ ክፍል ጋር ተያይዞ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ በጉልህ ተነግሮናል።
“በተሰጠን አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ስታዲየም በመጀመሪያ ዙር የግንባታ ምዕራፍ የመልበሻ ክፍሉ እና የመጫወቻ ሜዳውን እንዲሰራ አድርገናል። የመልበሻ ክፍሉም ሰፍ ብሎ ለ4 ቡድኖች እንዲሆን በሚያስችል ሁኔታ እየተገነባ ነው። ዋናው ሥራ የሜዳው ነው። እንደተገለፀው ሜዳው ተቆፍሮ ነበር። ግን በሀይማኖታዊ ጉዳዮች እና በክረምቱ ምክንያት የተቆፈረው ሜዳ እንዲደለደል ተደርጓል። የመልበሻ ክፍሎቹን ጨርሰናል። አሁን ወደ ሜዳው እና ወደ ተመልካች መቀመጫ እናመራለን።” ብለዋል።
በመቀጠል በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት እስካሁን ያለው አፈፃፀም በታሰበው ምልኩ አለመሄዱን፣ ስለ በጀት ጉዳዮች፣ የመጫወቻ ሜዳው የዝግጁነት ጊዜ፣ እንዲሁም ስታዲየሙ ለቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ይደርሳል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሾች ተሰጥተውባቸዋል።
በቅድሚያም አቶ አስመራ አፈፃፀሙን እና የመጫዎቻ ሜዳውን በተመለከተ “እውነት ለመናገር አፈፃፀሙ ዝቅተኛ አይደለም። ዋናው ካፍ ያስቀመጠው የሜዳው ጉዳይ ነው። ሜዳውን ግን ባልነው መንገድ ጀምረን አቆምነው። ሜዳው ስለቆመ ሁሉም ስራ ከሚቆም የመልበሻ ክፍሎችን መስራት ጀምረናል። ከመስከረም 15-20 ካሉት ቀናት ጀምሮ ደግሞ ሜዳውን መስራት እንጀምራለን። ሜዳው ከተቆፈረ በኋላ ከ3-4 ወራት ብቻ ሳር እንዲበቅል እንጠብቃለን። በአጠቃላይ ስታዲየሙ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲደርስ እንሰራለን።”
ከበጀት ጋር በተገናኘ ግንባታው መንጓተቶች ይኖሩበታል ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ችግር እንደማይኖር ተጠቁሞ የአዲስ አበባን የስፖርት ተመልካች በቶሎ ወደሚወደው ስፖርት ለመመለስ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
የጥያቄዎቹን መልስ በሚመለሱበት ጊዜ አቶ ዱቤ “እንደ መንግስት ፖሊሲ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት ስራዊችን እየሰራን ነው። ከታችኛው የወረዳ መዋቅር ጀምሮ እስከ ትምህርር ቤቶች ደረስ ታዳጊዎች የማዘውተሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው ማለት ነው። በዋናነት እኛ በፌዴራል ደረጃ የምንሰራው ስራ አለ። ክልሎች ደግሞ በየስራቸው ባለው መዋቅር ስራዎችን ይሰራሉ። በአጠቃላይ በ2013 በማዘውተሪ ስፍራዎች ግንባታ ጥሩ አፈፃፀም ነበረው። በ2014 2 ወይም 3 ዓለማ አቀፍ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች እንዲኖሩን እናደርጋለን።” ብለው ሀሳባቸውን በመስጠት መግለጫው ተጠናቋል።