ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ከአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጪ ሆኗል

Read Time:1 Minute, 44 Second

ሱዳን ላይ የተደረገው የአል ሂላል እና የፋሲል ከነማ የመልስ ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ አል ሂላል ከሜዳ ውጪ ባስቆጠረው ግብ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

የመልሱ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አል ሂላሎች በፊት አጥቂያቸው መሀመድ አብዱርሀማን አማካይነት በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ባደረጓቸው እና በሳማኬ በተያዙ ሁለት ሙከራዎች የጀመረ ነበር። በፋሲል በኩልም ከደቂቃዎች በኋላ በረከት ደስታ ከርቀት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ ምላሽ ሰጥቷል። በአመዛኙ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተው የቡድኖቹ እንቅስቃሴ ተመጣጣኝነት የሚታይበት ነበር። በቅብብሎቻቸው አደገኛ ዕድሎችን ባይፈጥሩም አል ሂላሎች በግራ መስመር አጥቂው አብዱል ራኡፍ ፋሲሎች ደግሞ በቀኝ በሽመክት ጉግሳ በኩል አመዝነው ለማጥቃት ቢሞክሩም ጨዋታው በሁለቱ ሳጥኖች መከል ተገድቦ የቆየ ነበር።

 

በዚህ ሁኔታ የቀጠለው ጨዋታ 23ኛው ደቂቃ ላይ ባለሜዳዎቹ በግራ ክንፍ በሰነዘሩት ጥቃት ጎል ተቆጥሮበታል። የመስመር አጥቂው ያስር ሙዘሚል ሰብሮ በመግባት አንድ የፋሲል ተከላካይን ቀንሶ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ መሀመድ አብዱርሀማን ከመረብ አገናኝቶታል። ከፋሲል ይልቅ የኳስ ቁጥጥራቸው ቶሎ ወደ ሳጥኑ ይደርስላቸው የነበሩት ሂላሎች ከአስር ደቂቃ በኋላ ሌላ ግብ ለማግኘት ከጫፍ ቢደርሱም ምስጋና ለአምሳሉ ጥላሁን ይግባና ሳይሳካላቸው ቀርቷል። አብዱል ራኡፍ በአስገራሚ ፍጥነት በግራ በኩል ሰብሮ ገብቶ ያስቀረለትን መሀመድ አብሩሀማን ሁለት ተከላካዮችን አሸማቆ ወደ ግብ ሲልከው ነበር አምሳሉ ከግቡ መስመር ላይ በግንባሩ ያወጣበት።

ቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ጨዋታው ግጭት እየበዛበት መጥቶ 42ኛው ደቂቃ ላይ በሽመልት ጉግሳ እና መሀመድ አብዱርሀማን ጉሽሚያ መነሻነት በተጫዋቾች መሀከል መጠነኛ ግርግር የታየበት ሆኖ ሌላ ግብ ሳይቆጠር ተቋጭቷል።

ከዕረፍት መልስ ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥሩ ሻል ብለው ቀርበዋል። ነገር ግን ግብ ለማግኘት መቃረብ የጀመሩት ሱዳኖቹ ነበሩ። 56ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙዘሚል በግል ፍጥነቱ ሳጥን ድረስ ኳስ ነድቶ ገብቶ ሲስት ከአንድ ደቂቃ በኋላ የአማካዩ ሳላ አድል ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በአብዱርሀማን ተሞክሮ ለጥቂት ወደ ወጪ ወጥቷል። ከእነዚህ ሙከራዎች በኋላ የተሻለ ኳስ በመያዝ የተጋጣሚያቸውን ፍጥነት ማርገብ እና ወደ ፊት ጠጋ ብሎ መንቀሳቀስ ችለዋል።

የፋሲሎች ወደ ሳጥኑ መቅረብ የቅጣት ምት አጋጣሚዎችን ሲያስገኝላቸው የቆየ ሲሆን 80ኛው ደቂቃ ላይም ግብ አስገኝቶላቸዋል። በረከት ደስታ ላይ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን የረጅም ርቀት ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው ያሻማል ተብሎ ሲጠበቅ የመታው ኳስ በተደራቢ ተጫዋች ተጨርፎ ከመረብ አርፏል። በተቀሩት ደቂቃዎች ሱዳንዊያኑ ኳስ በቶሎ በማራቅ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በማቀዝቀዝ እና በተደጋጋሚ በመውደቅ ውጤቱን ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ተጠናቋል።

በዚህም መሰረት የሱዳኑ አል ሂላል ከሜዳ ውጪ የተሻለ የግብ መጠን ያስቆጠረ በመሆኑ በድምሩ 3-3 ከተጠናቀቀው ጨዋታ ወደ ሁለተኛው የቅድመ ማጣሪያ ማለፍ የቻለው ክለብ ሆኗል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!