በአራት የዕድሜ እርከኖች መካከል ከሰኔ 3 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የሀላባ የክረምት ውድድር በደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተጠናቀቀ፡፡
ረጅም ዕድሜን እንዳስቆጠረ የሚነገርለት እና በበርካታ ተመልካቾች ፊት በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚደረገው የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የክረምት የእግር ኳስ ውድድሮች በአራት የዕድሜ እርከኖች መካከል ከሰኔ 3 ጀምሮ ሲደረግ ሰንብቶ በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ ከሰዓት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ 25 ዓመታትን ባስቆጠረው የዘንድሮ ውድድር ላይ ሰላሳ ቡድኖች በድምሩ ተካፋይ የነበሩ ሲሆን ትናንት ከፍተኛ የስፖርት አመራር እና የክብር እንግዶች በተገኙበት ከ17 ዓመት በታች የፍፃሜ ፍልሚያ ጨወታ በተደጋጋሚ የገዘፈ ታሪክ ያላቸው እና ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቁት ሀላባ ሸገር እና ቀይ ዛላ ተገናኝተው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ 1ለ1 ተለያይተው በተሰጠው የመለያ ምት ቀይ ዛላ 5ለ3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዚህኛው የዕድሜ እርከን የዋንጫ ባለቤት በመሆን አጠናቋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ባሉ ቀናት በሌሎች የእድሜ እርከኖች ጨዋታዎች ተደርገው የዋንጫ አሸናፊ ቡድኗች ታውቀውበታል፡፡ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮኑ ቀይ ዛላ ከ13 አመት በታች ሻምፒዮን ሲሆን ከ15 አመት በታች ገጠር ልማት ከ21 ዓመት በላይ ሀላባ ሸገር ሻምፒዮን መሆን የቻሉ ቡድኖች ሆነዋል፡፡
በየዓመቱ ተወዳጅነት በማትረፍ እና በበርካታ ደጋፊዎች መካከል በመደረግ በብዙሀኑ ዘንድ ሲደረግ በሰነበተው የሀላባ የክረምት ውድድር ላይ በክብር እንግድነት የከተማው ከንቲባ አቶ ሀሩና አህመድ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ውድድሩ ተጠናቋል። በንግግራቸውም መሰል ውድድሮች በከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ ለሆነው ሀላባ ከነማ እግርኳስ ክለብ መጋቢ ይሆን ዘንድ እና ተተኪ ተጫዋቾችን ለማፍራት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ውድድሩ ያለምንም የጸጥታ ችግር ውድድሩ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት በጠቅላላው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡