‹‹የቤት ስራችንን በሜዳችን መጨረስ ይገባናል›› በሃይሉ አሰፋ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር አማካይ በሃይሉ አሰፋ ዛሬ ረፋድ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደተዘጋጀ ተናግሯል፡፡
‹‹ ለጨዋታው በአእምሮውም በአካል ብቃቱም ዝግጅት አድርገናል፡፡ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ የምናደርግበት ጊዜው ደርሷል፡፡ በእግርኳስ ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ የሆነ ቡድን ያሸንፋል፡፡ ጥሩ የአሸናፊነት ታሪክ ያለው ቡድን ሁሉ ባለፈ ታሪኩ አያሸንፍም፡፡ ቲፒ ማዜምቤንም የምንመለከተው ከዚህ አነፃር ነው፡፡ ስለዚህ አቅልለንም አክብደንም ወደ ጨዋታው አንገባም፡፡›› ብሏል፡፡
የአምናው የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ከቲፒ ማዜምቤ አጨዋወት አንጸር ቅዱስ ጊዮርጊስ በምን አይነት አጨዋወት ወደ ሜዳ መግባት እንደሚኖርበትም ጠቁሟል፡፡ ‹‹በቲፒ ማዜምቤ ዙርያ ጥቂት መረጃዎች አሉን ፡፡ የቡድኑን እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ቪድዮዎችን በመመልከት በዛ ላይ ተመስርተን ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡ የሌሎች አፍሪካ ቡድኖች በአብዛኛው የሚታወቁት በአየር ላይ እና በአካል ብቃት ላይ በተመሰረተ አጨዋወት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኳሱን በህብረት ተጋግዘን የምንጫወት ከሆነ ይቸገራሉ፡፡ እናም ያንን ተንተርሰን እየሰራን እገኛለን፡፡››
በሃይሉ በመጨረሻም በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት በሚያደርጉት ጨዋታ የቤት ስራቸውን ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው ተናግሯል፡፡ ‹‹ የመጀመርያውን ጨዋታ በሜዳችን እናደርጋለን፡፡ የቤት ስራችንን መጨረስ ካለብንም የሚገባንም እዚሁ ሜዳችን ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ እግርኳስ ምን እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ ዋና የቤት ስራችን ይህ ነው፡፡ አሁን ላይ ሆነን ስለ መልሱ ጨዋታ የምናስብበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ በባህርዳር ስታድየም ያላቸውን ያለመሸነፍ ሪኮርድ ለማስጠበቅ እንጫወታለን፡፡›› ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

IMG_4835

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *