የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል

ከሩዋንዳ አቻው ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከፊቱ ያለበት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እና ከፊቱ ያሉበትን ጨዋታዎች አስመልክቶ ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥቷል።

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከፊቱ የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር እንደሚጫወት ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ለዚሁ የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሦስት ሳምንታት በፊት ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ የጀመረ ሲሆን ዓርብ ላለበት የመጀመሪያ ጨዋታም ነገ ጠዋት ወደ ስፍራው የሚያመራ ይሆናል። ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ ዋና አሠልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል መግለጫ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ዝግጅታቸውን አስመልክቶ ይህንን አጭር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ለሩዋንዳው የደርሶ መልስ ጨዋታ በቅድሚያ ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበን ነበር። ከባንክ ተጫዋቾች ውጪ 2 ተጫዋቾች በግል ምክንያት ስብስቡን አልተቀላቀሉም ነበር። ባለን ጊዜ ጥሩ ልምምድ ለመስራት ሞክረናል። በቅድሚያ 3 ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከዛም በድጋሜ ሌሎች 3 ተጫዋቾች በተመሳሳይ ጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። በአጠቃላይ ከጉዳት እና ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ 7 ተጫዋቾችን ቀንሰን ልምምዳችንን ስንሰራ ነበር።

“ባልተለመደ መልኩ የእድሜ ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ፌዴሬሽኑ ጥሩ ሥራዎችን እየሰራ ነው። ይህ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ደግሞ ለዋናው የሉሲዎቹ ቡድን ተጫዋቾችን የሚመግብ ነው። ለዚህ ደግሞ ልምድ ያስፈልጋል። በዚህ ስብስብ ውስጥ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ የነበሩ ከ10 በላይ ተጫዋቾችን አምጥተናል። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ይህ መተካካት የሚቀጥል ነው።” ብለዋል።

አጭር ደቂቃ ከፈጀው የአሠልጣኙ ማብራሪያ በኋላ ደግሞ በስፍራው የተገኙት በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል። በተለይ በውድድሩ ያላቸው እቅድ ምን እንደሆነ የተጠየቁት አሠልጣኝ ፍሬው “እቅዳችን ለዋናው ዓለም ዋንጫ ማለፍ ነው።” ብለው ምላሽ ከሰጡ በኋላ በተከታይነት የዝግጅት ጊዜው ማጠሩን አስመልክቶ ይህንን ብለዋል።

“ለጨዋታዎቹ የ22 ቀናት የዝግጅት ጊዜ አግኝተናል። እንደምታውቁት ተጫዋቾቹ ከእረፍት የመጡ ናቸው። ሴቶች ላይ ደግሞ ያለው ነገር ይታወቃል። ይህ ተፅዕኖ እንዳለ ቢሆንም ባለን አቅም የተሻለ ነገር ለመስራት ሞክረናል። የሚገርማችሁ ነገር በኪሎ መጨመር ሁሉ የቀነስናቸው ተጫዋቾች አሉ። በአጠቃላይ ለሩዋንዳው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ተዘጋጅተናል ብዬ ባላምንም ባለን ጊዜ በተቻለ አቅም ለመዘጋጀት ሞክረናል። የተሻለ ውጤትም ለማምጣት እንጥራለን።”

 

የጋዜጠኞችን ጥያቄ መቀበል የቀጠሉት አሠልጣኙ ከዝግጅት ጊዜው ማጠር ጋር ተያይዞ ተከታይ ጥያቄ ቀርቧላቸዋል። እሳቸውም በምላሻቸው “እኔ እንደ አሠልጣኝ እቅድ አለኝ። እቅዴንም ለፌዴሬሽን አስገብቻለሁ። ግን በእቅዴ መሰረት አልተኬደም። ይህ ቢሆንም ባለኝ ነገር ለመስራት ሞክሬያለሁ። ከውድድር የራቁ ተጫዋቾች በአንድ ጊዜ ለጨዋታ ማዘጋጀት በጣም ከባድ ነው። ግን እንደ አሠልጣኝ ባለን ነገር መፍትሄ ማምጣት አለብን። የዝግጅት ጊዜው እንደ ባለሙያ ያጥራል። ቢሆንም ባለን ነገር ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል።” ብለዋል።

በተከታይነት ስለተጋጣሚ ብሔራዊ ቡድን የሚያውቁት መረጃ ካለ ተብለው የተጠየቁት አሠልጣኙ “ስለ ተጋጣሚ ቡድን ምንም መረጃ የለንም። በኮቪድ ምክንያት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ስለሌሉ የሀገሪቷን ወቅታዊ ብቃት ለማየት አልቻልንም። ግን ከዚህ ቀደም ባለው ነገር ሩዋንዳ ኳስ የሚጫወቱ ናቸው። በተጨማሪም ፈጣን ልጆች አሏቸው። ግን እንደ ባለሙያ የአሠልጣኝ ልዩነት የሚታየው በጨዋታ ላይ የሚፈጠሩ ነገሮችን አይቶ ነገሮችን ማስተካከል ላይ ነው። ስለዚህ ባለው ነገር ጨዋታውን እንቀርባለን።”

ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር ተያይዞ ያለውን ግንኙነት በተከታይነት የተጠየቁት አሠልጣኙ “ከዋናው ቡድን ጋር በደንብ እንገናኛለን። ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮቪድ ስለነበረ ምንም ማረግ አልቻልንም። ከዚህ በኋላ ግን በደንብ እየተናበብን ለመስራት እና በቡድኖቹ መካከል ያለውን ተመጋጋቢነት ለማስቀጠል እንሞክራለን።” ብለዋል።

ተጫዋቾቹ በሰሩት እና በተዘጋጁት ልክ ነው መጠየቅ ያለባቸው የሚሉት አሠልጣኝ ፍሬው “ሴት ተጫዋቾች ልበ ሙሉ ናቸው። ተጫዋቾቹም ሆነ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ከፊታችን ያለውን ጨዋታ ለማሸነፍ ዝግጁ ነን።” ብለው የዕለቱን ጋዜጣዊ መግለጫ አገባደዋል።

ያጋሩ