ከነገ በስትያ የሚጀምረውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

ለ15 ጊዜ የሚደረገውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አስመልክቶ ዛሬ ረፋድ መግለጫ ተሰጥቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚከናወነው የመዲናው ዋንጫ ዘንድሮ ለ15 ጊዜ እንደሚከናወን ይታወቃል። በስምንት ክለቦች መካከል የሚደረገው የዘንድሮ ውድድርም ከመስከረም 15 ጀምሮ እስከ 30 ድረስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል። ባሳለፍነው ሳምንት የውድድሩ የምድብ ድልድል የወጣ ቢሆንም ተጋባዡ የደቡብ ሱዳን ክለብ ሙኑኪ ኤፍ ሲ እንደማይሳተፍ ከታወቀ በኋላ ጅማ አባጅፋር ተተኪ ቡድን መሆኑ ተሰምቷል። ይህንን እና አጠቃላይ የውድድሩን ይዘት በተመለከተ ዛሬ ረፋድ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ከተባለው ጊዜ እጅግ አርፍዶ (75 ደቂቃዎችን) በተጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አስራት (አሠልጣኝ)፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የማርኬቲንግ ክፍል ሀላፊ አቶ ደረጄ፣ የፌዴሬሽኑ አቃቤ ንዋይ አቶ ይገረም፣ የታዳጊ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን እና የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ከዳሽን ባንክ የአሞሌ ተወካዮች ጋር በመሆን ተገኝተዋል። በቅድሚያም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አስራት ኃይሌ ውድድሩን በተመለከተ አጠቃላይ ገለፃ አድርገዋል።

“ውድድሩ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ክለቦች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ክለቦች መካከል ነው የሚደረገው። በውድድሩ እንዲሳተፉ የጠየቅናቸውም ክለቦች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተውናል። እንደምታውቁት የአዲስ አበባ ስፖርት ቤተሰብ የስፖርት እንቅስቃሴ ጠምቶታል። ውድድር ካየ ቆይቷል። ስለዚህ በዚህ ውድድር ጥሩ ፍክክር እንዲኖር እና ደጋፊዎቹም የደመቀ ውድድር እንዲመለከቱ እየተሰራ ነው።

“የደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ክለቦች ይኖራሉ ብለን ነበር። ግን የኤርትራው ክለብ በፍቃድ ምክንያት የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ደግሞ እስከ ትናንት ወዲያ ድረስ ምላሽ ባለመስጠቱ በውድድሩ አይሳተፉም። በተለይ የደቡብ ሱዳኑ ክለብ መልሱ ዘገየና ሀገር ውስጥ ያሉ ክለቦችን ብቻ በማሳተፍ ለማድረግ ወስነናል። ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ስለደረሰም በኤርትራው እና በደቡብ ሱዳኑ ክለብ ምትክ ሌሎች ክለቦችን ተክተናል። በደቡብ ሱዳኑ ክለብ ምትክ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን ተክተናል።” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረው “የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ገቢው በዚህ የከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ነው። በዚህ ውድድር ላይ ገቢ ካላገኘን ደግሞ ዓመቱን ሙሉ የምንሰራቸውን ስራዎች ማከናወን አንችልም። የተሻለ ነገር ለማግኘትም በጣም ጥረናል። የደመቀ ውድድር እንደሚኖረንም አስባለሁ።” በማለት ሀሳባቸውን አገባደዋል።

በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት የዳሽን ባንክ የአሞሌ ተወካይ በውድድሩ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም የሚገቡበትን መንገድ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም የውድድሩ የመግቢያ ስርዓት ዘመናዊ ለማድረግ እና ደጋፊዎች በቀላሉ ያለ ሰልፍ ትኬት የሚቆርጡበትን መንገድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። በዚህም የስፖርት ቤተሰቡ በ2 አይነት መንገድ ትኬት መቁረጥ እንደሚችል ፣ 1 በስልኩ ቴሌግራም ላይ My amole Official bot’ን በመጠቀም 2 ደግሞ በሁሉም የአሞሌ የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በአካል ተገኝቶ መቁረጥ እንደሚችል ተጠቅሷል።

ከገለፃዎቹ በኋላ በስፍራው የተገኙት የብዙሃን መገናኛ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሾች ተሰጥተዋል። በተጠየቁት ጥያቄዎች መሠረት ለውድድሩ ስፖንሰር ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ሲገለፅ ከዚህ በፊት የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት እንኳን የሌለውን ተቋም (የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን) ለማስተካከል እየተሰራ እንደሆነ ተጠቁሟል። ከኮቪድ ጋር በያያዘ ምንም አይነት ግለሰባዊ ንክኪ እንዳይኖር እንደተሰራ፣ የጨዋታ ኮከብ በየጨዋታው እንደሚመረጥ እና ከበፊቱ በተሻለም ሽልማትም እንደሚበረከት እንዲሁም ስታዲየሙ ከሚችለው አቅም በግማሽ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንደሚገቡ እና የስታዲየም መግቢያ ትኬት ትናንት ማታ መሸጥ እንደተጀመረ በተጠየቁት ጥያቄዎች መሠረት ምላሾች ተሰጥተዋል። በመጨረሻም ለተሳታፊ ክለቦች ከሚገኘው ገቢ ክፍፍል እንደሚደረግ እና ለመከላከያ ሰራዊትም ከሚኖረው ገቢ ድጋፍ እንደሚደረግ ተብራርቶ ውድድሩ በአዲስ ቲቪ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ተነግሯል።

ውድድሩ ቅዳሜ ሲጀምር 8 ሰዓት አዲስ አበባ ከተማ ከመከላከያ 10 ሰዓት ደግሞ ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል።