ስድስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን አልተቀላቀሉም

ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከፈረሰኞቹ የመረጧቸውን ተጫዋቾች አላገኙም።

ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 7 ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አድርጎ ሦስት ነጥብ በማግኘት የምድቡ 3ኛ ደረጃ ላይ (ከጋና ጋር እኩል ነጥብ ቢይዝም በእርስ በእርስ ግንኙነት ውጤት ተበልጦ) ይገኛል። የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎችን ባለንበት ወር መጨረሻ የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ቢያቀርብም ፍቃድ ከተሰጣቸው 2 ተጫዋቾች ውጪ 6 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ስብስቡን እንዳልተቀላቀሉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

መስከረም 26 እና 30 ለሚኖሩት ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ከሁለት ሳምንት ያነሰ የዝግጅት ጊዜ በማውጣት ጥሪ ያስተላለፉት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በትናንትናው ዕለት 16 ተጫዋቾችን ማግኘታቸው ታውቋል። አስራ ስድስቱ ተጫዋቾች በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው ሪፖርት ካደረጉ በኋላም ወደ ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አምርተው አዳራቸውን እዛው እንዳደረጉ ተመላክቷል።

ነገርግን ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡት ምኞት ደበበ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ጋቶች ፓኖም፣ አቤል ያለው፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ቸርነት ጉግሳ ክለባቸው ሊለቃቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑን እንዳልተቀላቀሉ ተረጋግጧል። ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ አካል ለማድረግ ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ እንደሆነ ሰምተናል። ምናልባት ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የክለቡ አመራሮች በሚያደርጉት ንግግር ተጫዋቾቹ በቅርቡ ስብስቡን ሊቀላቀሉ እንደሚችል ተገምቷል።

ያጋሩ