ለኢንተርናሽናል ዳኝነት ያለፉ አዳዲስ ዳኞች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ልማት እና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በ2022 የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ የሚወስዱ ዳኞችን ዝርዝር ለፊፋ ልኳል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ልማት እና አስተዳደር ኮሚቴ ከቀናቶች በፊት በ2022 ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን  ሊመሩ ለሚችሉ ዳኞችን ለፊፋ ለማሳወቅ ለነባር ዳኞች የአካል ብቃት ፈተና እንዲሁም ደግሞ ከነባሮቹ በሚወድቁት ምትክ ለአዳዲስ ዳኞች የአካል ብቃት እና የፅሁፍ ፈተና ከአንድ ሳምንት በፊት አዘጋጅቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ነባር የሆኑ ሴት ዳኞች ዋና ዳኛ ፀሐይነሽ አበበ፣ መዳብ ወንድሙ እና ሊዲያ ታፈሰ እንዲሁም በረዳት ዳኝነት ይልፋሸዋ አየለ፣ ብርቱካን ማሞ እና ወይንሸት አበራ የተሰጠውን ፈተና በአግባቡ በመወጣታቸው በ2022 በኢንተርናሽናልነት የሚቀጥሉ ሲሆን የተሰጠው የአካል ብቃት ፈተና መውደቋ የተረጋገጠው አስናቀች ገብሬን በአዲስ ዳኛ ለመተካት በተሰጠው የአካል እና የፅሁፍ ፈተና በብቸኝነት የተወዳደረችውና በብቃት ማለፍ የቻለችው ምስጋና ጥላሁን በቦታው አስናቀችን ተክታ የ2022 ለኢንተርናሽናል ዋና ዳኛነት ተመርጣለች።

በተመሳሳይ ከሳምንት በፊት በወንዶች ነባር ዋና እና ረዳት ዳኞች በተሰጣቸው የአካል ብቃት ፈተና መሠረት አማኑኤል ኃይለሥላሴ ፈተናው ላይ ባለመገኘቱ፣ ብሩክ የማነብርሃን ደግሞ በፈተናውን በመውደቁ ከ2022 የዓለምአቀፍ ዳኞች ዝርዝር ውጪ መሆናቸው ሲረጋገጥ በዋና ዳኝነት ኃይለየሱስ ባዘዘው ፣ ለሚ ንጉሴ ፣ ባምላክ ተሰማ ፣ በላይ ታደሰ እና ቴዎድሮስ ምትኩ እንዲሁም በረዳት ዳኝነት ተመስገን ሳሙኤል ፣ ክንዴ ሙሴ ፣ ሸዋንግዛው ተባበል ፣ ፋሲካ የኃላሸት ፣ ይበቃል ደሳለኝ እና ትግል ግዛው በኢንተርናሽናል ዳኝነታቸው እንዲቀጥሉ ስማቸው ተልኳል። በዋና ዳኝነት አማኑኤል ኃይለስላሴ እና ብሩክ የማነ ብርሀንን ለመተካት በተዘጋጀው ፈተና ከሰባት ተወዳዳሪዎች አሸብር ሰቦቃ እና ማኑሄ ወልደፃዲቅ ከፍተኛውን ነጥብ በማምጣት ተመርጠዋል፡፡

በረዳት ዳኝነት ከሁለት ዓመት በፊት በዕድሜ ምክንያት ከዳኝነት የተገለለው በላቸው ይታየውን ለመተካት ከአራት ተወዳዳሪዎች መካከል ሙስጠፋ መኪ ከፍተኛውን ነጥብ በማምጣት ሲያልፍ ቀጣዩን ደረጃ የያዙት ዳንኤል ጥበቡ እና አበራ አብርደው በተለያዩ ምክንያቶች በፊፋ ተቀባይነት ላያገኙ የሚችሉ ረዳት ዳኞች ካሉ እነሱን ለመተካት ስማቸው መላኩ ታውቋል።

ፊፋ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላኩለትን ዳኞች ዝርዝር ተመልክቶ ውሳኔውን በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።