በነገው ዕለት ከሩዋንዳ አቻው ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አመሻሽ ላይ ሰርቷል።
ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ማለፉ አይዘነጋም። በዚህ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች የሩዋንዳ አቻውን የሚገጥመው ቡድኑም ከትናንት በስትያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ኪጋሊ አምርቷል።
20 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ስፍራው ያመሩት የቡድኑ አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤልም ስብስባቸው ስፍራው ከደረሰ በኋላም ቀለል ያለ ልምምድ ትናንት እንዲሰራ አድርገው ነበር። በኪጋሊ ኖብሊዛ ሆቴል ያረፉት ተጫዋቾችም ነገ 10 ሰዓት ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን በኪጋሊ ስታዲየም አመሻሽ ላይ አከናውነዋል።
ምስሎች – © Ethiopian Football Federation