የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እየተካፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ላለበት ጨዋታ የሊቢያ ዜግነት ያላቸው ዳኞች ተመድበዋል፡፡
በኳታር አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2022 የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ ከተደለደሉት ጋና እና ዚምባብዌ ጋር ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ያከናወነ ሲሆን በሦስተኛው የማጣርያ መርሀግብር መስከረም 29 በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ደቡብ አፍሪካን ይገጥማል፡፡ ይህንን ጨዋታ እንዲመሩ አራት ዳኞች ከሊቢያ ተመድበዋል፡፡
የ41 ዓመቱ ኢብራሂም ሙታዝ በመሐል ዳኝነት ሲመሩት በረዳት ዳኝነት አምሳድ አቲያ እና ካሚል ማጅዲ፣ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ሁራይዊዳህ አብዱልዋሂድ መሆናቸው ታውቋል። የዳኞች አሰሰር ሌስሊ ሊዮናርድ ከታንዛኒያ፣ የጨዋታው ኮሚሽነር ዩጋንዳዊው ሌቲ ማይክ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ዶ/ር በረከት ቦጋለ የኮቪድ ክትትል እና የጤና ቡድን ኦፊሰር በመባል ለጨዋታው ተመርጠዋል፡፡