የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዕጣ ድልድሉ በዛሬው ዕለት ወጥቷል

አምስት የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን ተሳታፊ የሚያደርገው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሌዊ ሪዞርት ተካሂዷል፡፡

በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት የ2014 የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል ስያሜ በአምስት የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች መካከል በሀዋሳ ከተማ ቀደም ተብሎ ከተያዘለት ቀን በአንድ ወደፊት ተስቦ ከመስከረም 15 ጀምሮ መደረግ ይጀምራል፡፡ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሌዊ ሪዞርት የአምስቱም ክለብ ተወካዮች በተገኙበት የዕጣ ማውጣት መርሀግብር ተከናውኗል፡፡

ከተያዘለት ሰዓት ዘግይቶ 11፡40 ሲል በጀመረው የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል የወጣቶች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አክሊሉ አለሙ በስፍራው ለተገኙት በሙሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ እግር ኳስ ወይንም ስፖርት ጥልቅ መሆኑን ጠቁመው ሀዋሳ ከተማም በዚህ ረገድ በርካቶችን በማፍራት የጎላ ሚና ያላት እንደሆነች በመግለፅ በስፍራው የተገኘውን አዲሱ የሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን በምሳሌነት ከገለፁ በኋላ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ለዚህ ውድድር መሳካት የድርሻውን እየተወጣ በመሆኑ ያላቸውን አክብሮት ጭምር በንግግራቸው ገልፀው ለተቋሙ በማንኛውም ወቅት ድጋፍ እንደሚያደርጉም በክልሉ ስም ጠቁመዋል፡፡

በመቀጠል የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል በዚህ የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተካፋይ ለሆኑ አምስት ክለቦች ለውድድሩ የሚለብሱትን መለያ ትጥቅ፣ የአምበሎች የመለያ ምልክት እና የክለቦቹ አርማን በስጦታ መልክ አበርክተዋል፡፡ ስራ አስኪያጁም ለክለቦቹ የተሰራው መለያ አካባቢያቸው ባለ መስህብ እና መገለጫ መሰረት የተዘጋጀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝዳንት አቶ አንበስ አበበ በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ጥሪውን ተቀብለው ለመሳተፍ ዝግጅቱ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ከገለፁ በኋላ “ጅማ አባጅፋር እወዳደራለው ብሎ መልስ በደብዳቤ ከገለፀልን በኋላ በመቅረቱ የተሰራላቸው መለያ ባክኗል ይህም በመሆኑ አዝነናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ውድድሩ ከመስከረም 16 ጀምሮ መደረግ ይጀምራል ተብሎ ቢታሰብም ቀኑ በአንድ ቀን ወደ ፊት እንዲገፋ ሆኖ ቅዳሜ መስከረም 15 እንዲጀመር ሆኗል፡፡ ከሰዓት ጋር በተገናኘ ለውድድሩ የቀረበው ደንብ ላይ ውይይት መደረግ ሳይችል የቀረ ሲሆን የውድድሩ ኮሚቴዎች ደንቡን ለየክለቡ በመስጠት ቅሬታ እና መስተካከል አለባቸው ብለው በሚያስቡት ላይ በስልክ መነጋገር ይቻላል በሚል ውይይቱ አልተደረገም፡፡

በመጨረሻም መክፈቻ በተለየ ስነ ስርአት ለማከናወን እንደታሰበ ገለፃ ተደርጎ የመዝጊያ ንግግር የሀዋሳ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ደርጊቱ ጫሌ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻም በዙር ለሚደረገው ለዚህ ውድድር የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተደርጎ ፕሮግራሙ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

የመክፈቻ ጨዋታ

ቅዳሜ መስከረም 15

ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ 8፡00