ወጣቱ አጥቂ የጅማ አባጅፋርን ዝውውሩን አጠናቋል

ከሳምንታት በፊት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርገው ዝውውር የከሸፈው ወጣቱ አጥቂ ጅማ አባጅፋርን ለመቀላቀል በቃል ደረጃ የተስማማበትን ስምምነት ህጋዊ አድርጓል።

ከኢትዮጵያ መድህን የወጣት ቡድን ተገኝቶ ዋናውን ቡድን ያገለገለው ወጣቱ አጥቂ መሐመድ ኑር ባለንበት የዝውውር መስኮት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይዘዋወራል ተብሎ በስፋት ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም። ነገርግን ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። ተጫዋቹ ወደ ፈረሰኞቹ የሚያደርገው ዝውውር ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ የቆየ ቢሆንም የአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ጅማ አባጅፋር መቀላቀል ምርጫው አድርጎ ከቀናት በፊት ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር።

ከአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮጵያ መድህን ጋር የአንድ ዓመት ቀሪ ውል የነበረው መሐመድ ውል ማፍረሻ የነበረውን 500 ሺ ብር ጅማዎች በመክፈላቸው መዳረሺያው ጅማ መሆኑ እርግጥ ሆኗል። ተጫዋቹም የውል ማፍረሺያውን በመክፈል መልቀቂያውን ከመድህን የወሰደ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶም የሁለት ዓመት ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።