ወላይታ ድቻ ረዳት አሰልጣኝ ሾሟል

ወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ረዳትን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡

አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማጣመር የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመቀመጫ ከተማው ሶዶ እየሰራ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በየትኛውም የቅድመ ውድድር ዋንጫ ላይ በበጀት እጥረት የተነሳ እንደማይሳተፍ ሶከር ኢትዮጵያ ያረጋገጠች ሲሆን በቀጣዩ ቀናት በሚገኙ የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታዎች ግን ራሱን ለመፈተሽ እቅድ ይዟል፡፡ እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ በዋና አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ዘላለም ማቲዮስ እየተመሩ የነበሩት የጦና ንቦቹ በዛሬው ዕለት በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መሪነት አሰልጣኝ ጣሰው ታደሰን ረዳት አሰልጣኝ አድርገው በአንድ ዓመት ውል ሾመዋል፡፡

በአየር ኃይል እግርኳስን በተጫዋችነት ከጀመረ በኋላ በመቀጠል በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን በግራ መስመር ተከላካይነት ተጫውቶ እግር ኳስን ካቆመ በኋላ በአሰልጣኝነት በቀድሞው የአንደኛ ሊግ ተሳታፊው ክለብ ቫይስ ኮሌጅ ምክትል አሰልጣኝ ፣ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 ዓመት በታች፣  በአንደኛ ሊጉ አዲስከተማ ክፍለ ከተማ በረዳት እና በዋና እና በኢትዮጵያ መድን ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በአሰልጣኝነት አገልግሏል፡፡ ከክለብ ባሻገር ከዚህ ቀደም የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ረዳት የነበረው አሰልጣኙ በ2014 የወላይታ ድቻ አዲሱ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን በዛሬው ዕለት ተሹሟል፡፡

ያጋሩ