ኪጋሊ ላይ ለዓለም ዋንጫ አንደኛ ዙር ማጣሪያ ሩዋንዳን የገጠመው የኢትዮጵያ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በጨዋታው ሙሉ ብልጫ የነበረው የብሔራዊ ቡድኑ ሙከራዎች በ3ኛው ደቂቃ ቤተልሄም በቀለ ከማዕዘን ምት በግንባሯ ባደረገችው ሙከራ የጀመረ ነበር። በቡድን ፍጥትነትም ሆነ በአካላዊ ቅልጥፍና ከተጋጣሚያቸው እጅግ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያዊያኑ በቅብብል ከሚመጡባቸው አጋጣሚዎች እንዲሁም ከሚነጥቋቸው ኳሶች መነሻነት ደጋግመው ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። በተለይም 12ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የተላካውን ነፃ ኳስ ቱሪስት ለማ አስቆጠረች ሲባል ለጥቂት የወጣባት አጋጣሚ ቀዳሚ ግብ ለመሆን የቀረበ ነበር። በአንፃሩ ሩዋንዳዊያኑ ከረጅም ርቀት ከሚነሱ የቆሙ ኳሶች ነበር የተሻለ ለግብ ይቀርቡ የነበረው።
በዚህ መልኩ በጀመረው ጨዋታ 19ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በቀጥታ የመታችው ኳስ በግብ ጠባቂዋ ሲመለስ እዛው ጋር የነበረችው ረድኤት አስረሰሳኸኝ ወደ ግብነት ለውጣ ሀገሯን ቀዳሚ አድርጋለች። ከግቡ በኋላ ባለሜዳዎቹ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ሳጥን ለመድረስ ሲጥሩ ቢታይም ለመልሶ ማጥቃት እና ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶች ሲዳረጉ ይታይ ነበር። 28ኛው ደቂቃ ላይም ከሌላ ፈጣን ጥቃት ረድኤት ከቱሪስት ለማ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብላ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ውስጥ አክርራ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝታለች።
እስከ ቀዳሚው አጋማሽ መገባደጃ ድረስ ሩዋንዳዎች ኳስ ይዘው ለመውጣት ሲጥሩ ቢታዩም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፍ ባለ ጫና ደጋግሞ ወደ ፊት መድረስ ችሎ ነበር። ሩዋንዳዊያኑ የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት ሂደቶች በማቋረጥ የተጠመዱባቸው ቀሪ ደቂቃዎች ሌላ ግብ ሳይታይባቸው ተጠናቀዋል።
ከዕረፍት መልስም የኢትዮጵያዊያኑ የጨዋታ የበላይነት ቀጥሎ ታይቷል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ አከታትሎ ጎሎችን አስቆጥሯል። 56ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከቀኝ የሜዳው ክፍል በመነሳት ከኳስ ጋር ወደ ግራኝ የሳጥኑ አቅጣጫ በመሄድ እና ተጫዋቾችን በማለፍ መትታ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥራለች። ረድዔት ከአንድ ደቂቃ በኋላ በሌላ ዕድል ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ሙከራዋ መክኖባታል። ያም ቢሆን ግን 63ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ መሀል ለመሀል የተሰነጠቀላትን ኳስ ወደ አራተኛ ግብነት መቀየር ችላለች።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቱሪስት ለማ አማካይነት አራት አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። ቡድናቸው ተዳክሞ የታዩት ሩዋንዳዊያኑ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደግብ ለመሄድ ከመሞከራቸው ባለፈ አደገኛ የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተጠባባቂ ተጫዋቾቻቸውን በመለወጥ ወደ ሜዳ በማስገባት ዕድል በሰጡባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎችም ቡድኑ አልፎ አልፎ ዕድሎችን ቢፈጥርም እንቅስቃሴዎቹ በአመዛኙ ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ አምስተኛ ግብ ማካል አልቻለም። ይሁን እንጂ ፍፁም የነበረው የጨዋታ የበላይነቱን እስከመጨረሻው አስቀጥሎ ጨዋታውን 4-0 በሆነ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል።