ባሳለፍነው ግማሽ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ዑመድ ከነብሮቹ ጋር ያለውን ቆይታ አራዝሟል።
የ2006 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ዑመድ ኡኩሪ በ2013 ግማሽ ዓመት ሀዲያ ሆሳዕናን ተቀላቅሎ እንደነበር ይታወሳል። የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች የነበረው ዑመድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ የእግር ኳስ ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ 2007 ላይ ወደ ግብፅ ሊግ አምርቶ አል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያን ከዛም ኤንፒ፣ ኤል-ኤንታግ ኤል-አርቢ፣ ስሞሀን እና አስዋን ለተባሉ ክለቦች አገልግሎ ነበር። ተጫዋቹ ዐምና ወደ ሀገሩ ተመልሶ ነብሮቹን ቢቀላቀልም ከደሞዝ ጋር በተያያዘ በውሉ መሠረት ክለቡን ሳያገለግል ቀርቶ ነበር።
የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከትናንት በስትያ ቢዘጋም የሀዲያ ሆሳዕና አመራሮች ተጫዋቹ ውሉን እንዲያድስ ሲያግባቡ ቆይተው ዛሬ አመሻሽ ላይ በክለቡ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ተስማምቶ ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።