ጅማ አባ ጅፋር አስቀድሞ አስፈርሟቸው እንደነበረ የተነገረላቸው ተጫዋቾች ዝውውራቸው እክል በማጋጠሙ በእነርሱ ምትክ በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ታውቋል።
የፕሪምየር ሊጉ የ2014 የውድድር ዘመን ከሳምንታት በኋላ በሀዋሳ ይጀመራል፡፡ ለዚህ ውድድር ጠንክሮ ለመቅረብ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር ከወራት በፊት አንጋፋው አጥቂ ሳላሀዲን ሰዒድን ለሁለት አመት አስፈርሞ የነበረ ቢሆንም የአጥቂው ዝውውር እክል ገጥሞታል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም ዓመታትን ያሳለፈው እና ባለፈው ክረምት አባ ጅፋርን መቀላቀሉ ተገልፆ የነበረው የሳላዲን ዝውውር ያጋጠመው እክል መፍትሔ እንዲያገኝ ክለቡ ጥረት እያደረገ ሲሆን ጥረቱ የማይሳካ ከሆነ ሳላዲንን ከጅማ አባጅፋር ጋር የማንመለከተው ይሆናል፡፡
በተያያዘም የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ የመስመር ተጫዋች ሱሌይማን መሀመድም በተመሳሳይ የጅማ ዝውውሩ እንዳልተሳካ ሰምተናል፡፡ በእርሱም ምትክ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በወላይታ ድቻ ያሳለፈው የመስመር ተከላካይ አስናቀ ሞገስን ለአንድ ዓመት የዝውውሩ ማብቂያ ሰዓታት ሲቀረው በድንገት ተጠርቶ መፈረሙ ታውቋል።
ሌላኛው ለጅማ አባ ጅፈር ለመጫወት ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ዩጋንዳዊው ግብጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ወደ አባ ጅፋር የሚያደርገው ዝውውር ጉዳይ አሁን አንዳማይሳካና በሁለተኛው ዙር መጫወት እንደሚችል በመነገሩ በእርሱ ምትክ ከኢትዮጵያ መድን የተገኘው ወጣቱ ግብጠባቂ ታምራት ዳኜን በመጨረሻ ሰዓት አስፈርሟል፡፡
በመጨረሻም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ለመጫወት ተስማምቶ የነበረው ወጣቱ አማካይ ሚካኤል ሀሲሳ ከቡድኑ መቀነሱን ሰምተናል።