ያለፉትን ሀያ ቀናት አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ሲያወዳድር የቆየው አርባምንጭ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ የሆነው አርባምንጭ ከተማ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርዶ የነበረ ቢሆንም የሊጉ ተሳታፊዎች ቁጥር ከፍ በማለቱ በድጋሚ በአንደኛ ዲቪዚዮን ይቀጥላል። ይህን ተከትሎም ክለቡ ከሌላው ጊዜ አንፃር ተጠናክሮ ለመቅረብ በማሰብ ረጅም አመት በቆየው አሰልጣኝ ጌታሁን ምትክ ሊሆን የሚችል አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሀያ ቀናት በፊት ክለቡ የቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ከአስር በላይ አሰልጣኞች ሲወዳደሩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻም አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ በዋና አሰልጣኝነት የአንድ ዓመት ውል የአዞዎቹ እንስቶችን ለማሰልጠን ፊርማውን እንዳኖረ አቶ ስንታየው ንጉሤ የክለቡ ስሥ አስኪያጅ ለድረገፃችን አረጋግጠዋል፡፡
በሴቶች እግር ኳስ ስኬታማ ከሆኑ አሰልጣኞች ተርታ የሚመደበው አሰልጣኝ ዮሴፍ ከ2004 ጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት ሀዋሳ ከተማን በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ የነበረ ሲሆን በክለቡ ቆይታውም ሁለት ጊዜ ያህል በፕሪምየር ሊጉ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሀስ ተሸላሚ ሁለት ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ የሴቶች ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን እንዲሆን ክለቡን አስችሏል፡፡ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በዞን ተከፍሎ በሚደረግበት ወቅት ሦስት ጊዜ ያህል የደቡብ ምዕራብ ዋንጫን ከዚህ ቀደም ለሀዋሳ አስገኝቶ የነበረው አሰልጣኙ የአርባምንጭ ከተማን የቅጥር ማስታወቂያ አሟልቶ በመገኘቱ በዛሬው ዕለት ለክለቡ ፊርማውን አኑሯል፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከአሰልጣኙ ቅጥር በፊት የአስር ነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙ ይታወሳል፡፡