ሉሲዎቹ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ከኢትዮጵያ 15 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አከናውኖ ድል አድርጓል።

ጥቅምት 10 እና 16 ከዩጋንዳ አቻው ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሳምንት በፊት በካፍ የልህቀት ማዕከል ዝግጅቱን መጀመሩ ይታወቃል። ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች ውጪ ያሉት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከውድድር በመራቃቸው ወደ ጥሩ የአካል ብቃት እንዲመጡ ጠንከር ያሉ ልምምዶችን በቀን ሁለት ጊዜ ሲያሰሩ ሰንብተዋል። በዛሬው ዕለት ደግሞ የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታቸውን ከ2 ዓመታት በፊት በአሠልጣኝ ኤርሚያስ እየተመራ ወደ ቻይና ከተጓዘው የኢትዮጵያ ከ13 በታች የወንዶች ብሔራዊ ቡድን (አሁን ከ15 ዓመት በታች) ጋር አድርገዋል።

የቡድኑ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በአብዛኛው ከውድድር የራቁ ተጫዋቾችን በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተው ጨዋታውን ቀርበዋል። በዚህም ቤተልሔም ዮሐንስ፣ ሳራ ነብሶ፣ ሴናፍ ዋቁማ፣ ኤደን ሽፈራው፣ መስከረም ኮንካ፣ እፀገነት ብዙነህ ፣ ሲሳይ ገብረዋህድ፣ ሥራ ይርዳው፣ ቤዛዊት ተስፋዬ፣ ቅድስት ዘለቀ እና የውብዳር መስፍን በቅድሚያ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በአሠልጣኝ ኤርሚያስ የሚመሩት የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ብልጫ ኖሯቸው ሲጫወቱ ያስተዋልን ሲሆን ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ ግን ተዳክመው ታይተዋል። ሉሲዎቹ በአንፃራዊነት በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት እስከ 36ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሥራ ይርዳው ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብ መትታ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

ከእረፍት መልስ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረው የገቡት አሠልጣኝ ብርሃኑ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት ይዘዋል። በተለይ ሴናፍ፣ ሎዛ እና መዲና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን ሲያደርጉ ታይቷል። በ58ኛው ደቂቃም ተቀይራ እስከወጣችበት ደቂቃ ድረስ ጥሩ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥን ውጪ ግብ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጋለች።

ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ሲጫወቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በበኩላቸው በቶሎ ግብ ለማስቆጠር ካላቸው ፍላጎት ከወገብ በላይ መጣደፍ የተሞላበት አጨዋወት ሲያደርጉ ታይቷል። ይህንን ተከትሎ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታውን አገባደዋል።

ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እጅግ ተስፋ ያሳዩትን የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ቡድን አባላት ሲያበረታቱ እና ሲመክሩ እንዲሁም ከጎናቸው እንደሆኑ ሲናገሩ አስተውለናል።

 

ያጋሩ