የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል

በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ከሩዋንዳ አቻው ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል።

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የዓለም የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ከሩዋንዳ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከቀናቶች በፊት ከሜዳው ውጪ አራት ለባዶ አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል። የመልሱን ጨዋታ የፊታችን ረቡዕ ባህር ዳር ላይ የሚያደርገው ቡድኑም ዝግጅቱን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል።

የቡድኑ ተጫዋቾች ከሩዋንዳ ከመጡ በኋላ ማረፊያቸው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በማድረግ የጂም ሥራዎችን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ከሦስት ቀናቶች በፊት ደግሞ እዚሁ መዲናችን በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል የሜዳ ላይ ልምምድ ማድረግ ጀምረው ነበር። በማግስቱ (ሀሙስ) ደግሞ ጨዋታውን ወደሚያደርጉበት ባህር ዳር በማምራት መደበኛ ልምምዳቸውን ጀምረዋል።

በቀን አንድ ጊዜ የሜዳ ላይ ልምምድ የሚሰሩት ተጫዋቾቹም በሦስተኛ ቀን የባህር ዳር ቆይታቸው ለአንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃዎች የቆየ ልምምዳቸውን ከ5 ሰዓት ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውነዋል። እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስም ምንም የጉዳት ዜና ቡድኑ ላይ እንደሌለ ተጠቁሟል። ማረፊያውን በኦሊቭ ሆቴል ያደረገው ቡድኑም እስከ ጨዋታው ዋዜማ ድረስ በተመሳሳይ ሰዓት ልምምዱን ከሰራ በኋላ ረቡዕ 10 ሰዓት ከሩዋንዳ ጋር የመልስ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና በሜዳቸው አራት ጎል አስተናግደው የማለፍ ተስፋቸው የጠበበባቸው ሩዋንዳዎች ነገ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ በማድረግ በተያያዥ በረራ ከአዲስ አበባ ባህር ዳር እንደሚገቡ ታውቋል።

ያጋሩ