የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የሦስተኛ ዙር ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ የተደረጉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን ሰበታ ከተማ ሲዳማ ቡናን አሸነፈዋል፡፡
ሀዋሳ ከተማ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ
ቀዳሚው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ 4፡00 ሰዓት ረፋድ ላይ አገናኝቷል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ብልጫ ጎልቶ በታየበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሀዋሳዎች በርካታ ሙከራዎችን በማድረግ በተደጋጋሚ የድሬዳዋን የግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውለዋል፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል ከመሀል ሜዳ በሚነሱ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የታዩ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ መድሀኔ ብርሀኔ እና አጥቂው ብሩክ በየነ ሲያደርጉት የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቡድኑ ለወሰደው ብልጫ ማሳያ ነበር፡፡ ሀዋሳዎች መድሀኔ ብርሀኔ በቀኝ በኩል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ባደረጋት ሙከራ ሀዋሳዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል፡፡በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች አብዱራህማን ሙባረክን ኢላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን አጥቂውም የሀዋሳን የመከላከል አደረጃጀት ስህተት ለመጠቀም የሞከረባቸው ሂደቶች ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ከመስመር ተሻግሮለት 10ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር ገጭቶ ብረት የመለሰበት ተጠቃሿ ሙከራ ነች፡፡
በብሩክ በየነ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ዕድልን ለመፍጠር ያልተቸገሩት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ልጆች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግብተዋል። ወንድማገኝ ኃይሉ ከብሩክ በየነ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው ብሩክ አክርሮ ሲመታ እና የግቡ ብረት ሲመልስበት በቃሉ ገነነ እጅግ ግሩም ጎል ፍሬው ጌታሁን መረብ ላይ አሳርፎ ሀዋሳን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች በማማዱ ሲዲቤ እና አብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትን ቢሆንም ወደ ግብነት ለመለወጥ ግን ተቸግረዋል፡፡ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በብሩክ በየነ እና ተባረክ ኢፋሞ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን መጠቀም አልቻሉም፡፡
ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝነት ያለውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ብናይም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለ ነበር፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች በዚህኛው አጋማሽ በብሩክ በየነ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና በቃሉ ገነነ አማካኝነት ያለቀላቸውን ዕድሎች ሲፈጥሩ ተመልክተናል፡፡59ኛው ደቂቃ ላይ በቃሉ ገነነ ከብሩክ በየነ ጋር በፈጠረው ጥሩ ስብጥር ብሩክ በመጨረሻም በቀላሉ አስቆጠረው ሲባል ስቶታል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ብሩክ ቃልቦሬ የሰጠውን ኳስ አብዱራህማን ሙባረክ ድሬዳዋን አቻ ለማድረግ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ጋናዊው ግብ ጠባቂ መሀመድ ሙንታሪ በሚገርም ብቃት አውጥቶበታል፡፡ 75ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው ንትርክ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ጨዋታውም በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳው አጥቂ ብሩክ በየነ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ሲዳማ ቡና 1-2 ሰበታ ከተማ
ከሰዓት 9፡00 ሰዓት ሲል እጅጉ ብርቱ ፉክክር ያስመለከተን የሲዳማ ቡና እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ ጅምሩን አድርጓል፡፡በታክቲክ የታጠረ የሜዳ ላይ ውጥረት በጉልህ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡና መሀል ሜዳ ላይ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ መውሰድ ችሏል። ይያም ቢሆን ሰበታ ከተማዎች ለውሳኔ እጅጉን ፈጣን ሆነው መገኘታቸው የሲዳማ ቡና የመከላከል ስህተት በመጠቀም ጎል ለማስቆጠር ቀዳዳ በመፈለጉ ረገድ ስኬታማዎች አድርጓቸዋል። በዚህም ሂደት 16ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በሳጥን ውስጥ የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ወጣቱ አማካይ አብዱልሀፊቅ ቶፊክ አስቆጥሮ ሰበታን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ጌቱ ኃይለማርያም ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ መልሶበታል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች ለማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጤታማ መስሎ ቢታይም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ግን ውስንነት ይታይባቸው ነበር፡፡ ከቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ የተገኙትን ሁለት ዕድሎች መትቶ ለአለም ብርሀኑ በቀላሉ ከያዘበት ውጪ ይሄ ነው የሚባል የጠሩ ዕድሎችን ቡናማዎቹ መፍጠር አልቻሉም፡፡ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጂኒያስ ናንጄቤ ከቀኝ መስመር ሲያሻማ ወጣቱ አጥቂ መሀመድ አበራ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ሰበታ ከተማዎች ጥንቃቄ አዘል የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራቸው ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ግቦችን በማስቆጠር ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ ብርቱ ጥረት ያደረጉበት ነበር፡፡ሲዳማ ቡና በፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሰ አማካኝነት ግቦችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲፈጥር የተመለከትን ሲሆን ኳሶች ይደርሱት የነበረው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ያለመጠቀሙ ቡድኑን የኋላ ኋ።ላ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ 62ኛው ደቂቃ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ወጣቱ አጥቂ መሀመድ አበራ ለሰበታ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የቡድኑ የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል፡፡82ኛው ደቂቃ ላይ ኬኒያዊው የመስመር አጥቂ ፍራንሲስ ናብራ ሲዳማ ቡናን ከሽንፈት ያላዳነች ግብ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው 2-1 ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሰበታ ከተማው መሀመድ አበራ የጨዋታው ምርጥ ተብሎ ተሸልሟል፡፡