የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከሁለት ቀናት በፊት ከመዘጋቱ በፊት ሲዳማ እና ሰበታ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ታውቋል።
ለ83 ቀናት የቆየው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከትናንት በስትያ መዘጋቱ ይታወቃል።መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ደግሞ ሲዳማ ቡና በኦንላይን አስመዝግቦት የነበረውን ኬንያዊ የመስመር አጥቂው ፍራንሲስ ካሀታን አስፈርሟል፡፡ ለሀገሩ ክለብ ቲካ ዩናይትድ የክለብ ህይወቱን ከጀመረ በኋላ በመቀጠል በደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ፣ በአልባኒያው ቲ ኤፍ ቲራና እንዲሁም በድጋሚ ወደ ሀገሩ ኬንያ ተመልሶ ለጎር ማሂያ ከተጫወተ በኋላ ባለፈው ዓመት ወደ ታንዛንያ በማምራት ለሲምባ በመጫወት ላይ የነበረው ይህ ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለ ሲሆን ዛሬ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ሲዳማ ቡና በሰበታ ከተማ 2ለ1 ሲረታ ተጫዋቹ ተቀይሮ በመግባት ለሲዳማ ቡና ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡
እንደ ሲዳማ ሁሉ ሰበታ ከተማም መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የአክሊሉ ዋለልኝን ዝውውር አጠናቋል። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ጅማ አባጅፋር እና ስሑል ሽረ ተጫዋች 2012 ክረምት ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩ ቢቀላቀልም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር ክለቡ በሊጉ ባለመሳተፉ ሳይጫወት ቀርቶ ነበር። አሁን ግን ከበርካታ ወራት በኋላ ዳግም በሊጉ ከመጫወት ሰበታ ከተማን በመቀላቀል በዛሬው ዕለት ከአዲሱ ክለቡ ጋር ልምምድ መስራት ከመጀመሩ ባሻገር ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተደርጓል።