ቆይታ ከፍቅሩ ተፈራ ጋር…

👉 “በጊዜው ትልቅ በነበረው 10 ብር የመጀመሪያ ዝውውር አድርጌያለው”

👉 “…ከዛ ከጓደኞቼ ጋር ተመካከርንና ስም ሲጠራ ባልመጣ ሌላ ሰው አቤት ብለን እንግባ ተባባልን”

👉 “በነገራችን ላይ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ምንም ነገር አልፈራም”

👉 “ህይወቴን በሙሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ ነው የኖርኩት”

👉 “እኔ ራሴን እየደገፍኩ ነው ያደኩት”       

ብዙዎች በራስ መተማመኑ ያስገርማቸዋል። ልበ ሙሉም ነው ይሉታል። ከምንም በላይ ግዙፉ ሰውነቱ ገና ስሙ ሲጠራ ዐይናቸው ላይ ብቅ ይላል። አዲስ አበባ መሐል ልደታ በጨርቅ ኳስ የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱም በደቡብ አፍሪካ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፊንላንድ፣ ቬትናም፣ ባንግላዲሽ እና ማሌዢያ አድርጎ ህንድ ላይ ፍፃሜውን አግኝቷል። የተለዩ አስደናቂ ጎሎችን የሚያስቆጥረውና በደስታ አገላለፁ የሚታወቀው የዛሬው እንግዳችን በሀገራችን ሚዲያዎች እምብዛም ባይታይም ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታዋለች። ፍቅሩ ተፈራ ለሜሳ!

ቁመታሙ አጥቂ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ እግርኳስ የወጣ ፍሬ ቢሆንም በአዳማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ከሦስት የማይበልጡ ዓመታትን አሳልፎ መዳረሻው ውጪ ሆኗል። ከአስር በላይ ክለቦችን በተለያዩ አህጉሮች እየዞረ ያገለገለው ፍቅሩ ከመነሻው ጀምሮ ያሳለፈውን የእግርኳስ ህይወት፣ ተሞክሮውን፣ የአኗኗር ዘይቤውን፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ እና እቅዶቹን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ሰፋ ያለ ቆይታ አንስቷል። መልካም ንባብ!

ትውልድህ እና እድገትህ የት ነው? ስለ ቤተሰብህም አያይዘህ ንገረን ?

ትውልዴ አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ በተለምዶ ስሙ ቶሎሳ ሰፈር በሚል ቦታ ነው። እድገቴ ደግሞ እዚሁ አዲስ አበባ አየር ጤና ነው። ቤት ውስጥ አምስት ነን። አራት ወንድሞች አሉኝ። አባቴ ተፈራ ለሜሳ ይባላል። እናቴ ደግሞ ንጋቷ ዘረፉ ትባላለች። እኔ ለቤቱ አራተኛ ልጅ ነኝ። በጣም ደስ ከሚል ቤተሰብ ነው የወጣሁት።

አስተዳደግህ ምን ይመስላል?

በጥሩ ቤተሰብ ነው ያደኩት። በአስተዳደጌ በተደረገልኝ ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። ቤተሰቦቼም በጣም ያበረታቱኝ ነበር። እናት እና አባቴን ብዙም ሳላድግ ነው ያጣኋቸው። እነሱ ካለፉ በኋላ ግን ወንድሞቼ በጥሩ ሁኔታ አሳድገውኛል። በዚህ አጋጣሚ ወንድሞቼን ማመስገን እና ለእነሱ ትልቅ ክብር እንዳለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። እንደ እናት ሆና ያሳደገችኝም ስኳሬ ንጉሴ ትባላለኝ። እሷንም ማመስገን እፈልጋለሁ። በአጠቃላይ እዚህ እንድደርስ በተለይ ወንድሞቼ በጣም ደግፈውኛል። በእነሱም ማበረታታት እና ድጋፍ ነው እዚህ የደረስኩት።

ስለ እግርኳስ አጀማመርህ ደግሞ አጫውተን?

እግርኳስን የጀመርኩት ሰፈር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች ነው። እኛ ታዳጊ እያለን አየር ጤና አካባቢ የተለያዩ አማራጭ መጫወቻ ሜዳዎች ነበሩ። እና ሜዳ ላይ ስጫወት የሰፈር ሰዎች ያዩኝ ነበር። በሰፈራችን ደግሞ የተለያዩ ውድድሮች ሲዘጋጁ ከእኔ ከፍ የሚሉ ሰዎች በሚሳተፉበት ግጥሚያ ላይ መርጠውኝ መጫወት ጀመርኩ። እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ከእድሜ ታላላቆቼ ጋር እየተጫወትኩ ብቃቴን ማሳየት ጀመርኩ። የሰፈር ሰዎች ብቃቴን አይተውም ክለብ መግባት እንዳለብኝ ነገሩኝ። እኔም ከዛ በኋላ እየበረታሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በምከታተልበት ባስሊዮስ እግርኳስን እየተጫወትኩ ራሴን ማጎልበት ቀጠልኩ። ከዛም አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባም የሰፈር ሰዎች የሰጡኝን ስንቅ እንደ ሞራል እየተጠቀምኩ መጫወት ቀጠልኩ። ከትምህርት ቤት ውድድሮች ጎን ለጎን ቀድሜ እንዳልኩት በአካባቢያችን በሚዘጋጁ ውድድሮች እሳተፍ ነበር። ከሌሎች ሰፈር የሚመጡ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር በተለምዶ ናትራን ሜዳ ይደረግ ነበር። እንደውም በግዢ አዲስ ክለብን መቀላቀል የጀመርኩት ያኔ ነው። በጊዜው ትልቅ በነበረው 10 ብር የመጀመሪያ ዝውውር አድርጌያለው። ሰፈሬ አየር ጤና ነው ግን የካራ ቆሬ ሰፈር ልጆች እኛ ጋር መተህ ተጫወት ሲሉኝ በጠቀስኩት ብር ዝውውር አድርጌ ቡድኑን ተቀላቀልኩ። በውድድሩም ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ ተሸልሜያለሁ። ቡድኑም ዋንጫ አነሳ። ከዚህ በተጨማሪ በተለምዶ አለርት ሜዳ በሚባለው ቦታም ትልቅ ውድድር ነበር። ከምታስበው በላይ ሰዎች በስፍራው ተገኝተው ጨዋታዎችን ያዩ ነበር። እዚህም ላይ ራሴን በደንብ አሳይ ነበር። ከዚህ አንስቶ የእግርኳስ ህይወቴ ሀ ብሎ ተጀመረ።

ስለዚህ የመጀመሪያው የእግርኳስ ህይወትህ የዝውውር ሂሳብ 10 ብር ነው?

አዎ። እንዳልኩህ ትልቅ ክለብ አይደለም። የሰፈር ውስጥ ቡድን ነው።  በጊዜው ደግሞ 10 ብር ትልቅ ነበር። ለዛች ውድድር ብቻ አገልግያቸው ነው የተለያየነው። እንደውም አሁን ላይ አንዳንድ የቅርብ ሰዎች ‘አንተ እኮ ተሽጠህ መጫወት የጀመርከው ድሮ ነው’ ይሉኛል። እንግዲህ በዚህች ገንዘብ ተጀምሮ ነው አውሮፓ ድረስ ሄጄ እንድጫወት የሆነው።

ማንን እየደገፍክ ነው ያደከው?

እኔ ራሴን እየደገፍኩ ነው ያደኩት። ይሄንን አሁን ሳይሆን ከድሮም ጀምሮ ስለው የነበረ ነገር ነው። የትኛውም ክለብ ላይ ራሴው ገብቼ ሰዎች ይደግፉኝ እንጂ እኔ የምደግፈው የለም። የውጪ ሊጎችን እከታተላለሁ። የእንግሊዝ፣ ስፔን እና የጣሊያንን ሊጎች አያለሁ ግን የምደግፈው ክለብ የለም። ሚቾ የሚለው ነገር አለ። እሱም ‘ሜዳ ላይ የምትጫወትበትን ቦታ እይ’ የሚለው ነው። እኔም ጨዋታዎችን ሳይ ይሄንን አስተውላለው። ሚቾ እንደውም እኔን ቶሬስ ነው የሚለኝ። እኔም የቶሬስን አጨዋወት እና እንቅስቃሴን አይ ነበር። ጥያቄህን ስቋጨው ታዳጊዎችም ራሳቸውን እየደገፉ እንዲያድጉ ነው ማስተማር የምፈልገው።

ፈርናንዶ ቶሬስን ትወደዋለህ?

በመውደድ ከሆነ ሮናልዶ ዴ ሊማን እወደዋለሁ። ምክንያቱን እሱ ያለው ጉልበት እና ፍጥነት የሚገርም ስለሆነ። ሚቾም ቶሬስ የሚለኝ አቋማችን አንድ አይነት ስለሆነ ነው።

ወደ ክለብ ህይወትህ ደግሞ እናምራ እስቲ የመጀመሪያው ክለብህን እንዴት ተቀላቀልክ?

መጀመሪያ ፕሮጀክት ተብሎ በጊዜው መስቀል አደባባይ ላይ ጥሪ ይተላለፍ ነበር። እኔ ደግሞ ይህንን የሰማሁት ዘግይቼ ነበር። አራት አምስት ሆነን ከሰፈር ልጆች ጋር ወደ ስፍራው አመራን። ግን ስንሄድ ረፍዶ ነበር። ምዝገባውም አልቆ ነበር። ወደ ፕሮጀክቱ የሚገባውም የተመዘገበ ብቻ ነው ተባለ። ከዛ ከጓደኞቼ ጋር ተመካከርን እና ስም ሲጠራ ባልመጣ ሌላ ሰው አቤት ብለን እንግባ ተባባልን። በነገራችን ላይ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ምንም ነገር አልፈራም። እነሱ ትንሽ ፈሩ መሰለኝ እኔ እንድቀድም ተደረገ። ከዛ ስም ሲጠራ አቤት የሚል ሲጠፋ እኔ ነኝ ብዬ ገባሁ። ቀሪዎቹ አራቱ ጓደኞቼም በተመሳሳይ መንገድ ገቡ። ግን የሚገርምህ በኋላ አምስታችንም ተያዝን። ቢሆንም ከስንት ሺ ልጆች ሰማንያ ልጆች ሲቀሩ ጓደኞቼ ወድቀው እኔ ብቻ አለፍኩኝ። በጊዜው ትውልድህን አድን የሚባል ቡድን ነበር። እነሱ ጋር እንድጫወት አስገቡኝ። ቡድኑን ጋሽ ይተፋ ነበሩ የሚያሰሩት። ከዛ በኋላ ደግሞ ወደ ክልል 14 ፖሊስ አመራሁ። በወቅቱ ክልል 14 ፖሊስ አበበ ቢቂላ ላይ ነበር ውድድር የሚያደርገው። አበበ ቢቂላ ስጫወት ደግሞ ብዙ ክለቦች ያዩኝ ጀመር። በጊዜው የቤተሰብ ታክሲ ነበር። በዛ ታክሲ እኔ ስራ እሰራ ነበር። ከወንድሞቼ ጋር እየተፈራረቅን ስለምንሰራ ጨዋታ ሲኖረኝ ወደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እሄዳለሁ። ታክሲው ትንሽም ቢሆን ገቢ ስለሚያስገኝ ትኩረቴ ወደ እዛ ነበር። ቢሆንም ባለኝ ጊዜ ወደ ሜዳ እየሄድኩ እጫወት ነበር። ቅድም እንዳልኩህ ሰፈር እያለሁ ትልልቅ ሰዎች ነበር የሚያበረታቱኝ። እዚህም (አበበ ቢቂላ ስታዲየም) በጣም ትላልቅ ሰዎች ሞራል ይሰጡኝ ጀመር። በዚህ አጋጣሚ ተስፋዬ ገብሬ ያየኛል። እሱም ወደ አዳማ እንድመጣ ይጠይቀኛል። እኔም እሺ ብዬ 1996 ላይ አዳማን ተቀላቀልኩ። ከክለቡ ጋር በነበረኝ ቆይታም በጣም ጥሩ ብቃት ነበር ያሳየሁት። ባሳየሁት ብቃት ደግሞ በዛኑ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ወደ ስብስባቸው እንድገባ ጥያቄ አቀረቡልኝ። እንደምታውቁት ሁለቱም ክለቦች በሀገራችን አሉ የሚባሉ አንጋፋ ክለቦች ናቸው። የሚገርመው ሁለቱም ክለቦች ገና በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ነበር ጥያቄ ያቀረቡልኝ። የእነሱ ጥያቄም ሞራል ሆኖኝ የበለጠ እንድሰራ አደረጉኝ። መጨረሻ ላይ 1997 ላይ ወደ ጊዮርጊስ አመራሁ።

ጊዮርጊስን እንደተቀላቀልኩ አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ አቀረበልኝ። ጊዮርጊስ ከገባው በኋላ በክለቤም ሆነ በብሄራዊ ቡድን ዋንጫ አገኘሁ። በቀጣዩም ዓመት ሩዋንዳ ላይ በብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ውድድር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ አገባደድኩ። በክለቤም በተከታታይ ዋንጫ አነሳሁ። ከዛ በዚሁ ዓመት ከግብፅ ክለቦች ጥያቄዎች ቀረቡልኝ። ክለቦቹም ቪዛ እና የአውሮፕላን ትኬት ይልኩ ነበር። የዛኔ ሁሉን ነገር የሚከታተልልኝ ወንድሜ ሰለሞን ነበር። አምስት ስድስት ክለቦች እንዳልኩህ ቪዛ ይልኩልኝ ነበር። በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ የነበረው ሚቾ ‘አንተ ትልቅ ቦታ መድረስ ትችላለህ። ከግብፅ የተሻለ ሀገር ሄደህ መጫወት ትችላለህ።’ ብሎኝ ሞራል ሰጥቶኝ ወደ ግብፅ እንዳልሄድ ሆነ። ሁሉ ነገሬን ተችዬ የነበረ ቢሆንም በሚቾ ምክር ጉዞዬን ተውኩት። ከዛ ታንዛኒያ ላይ በሚደረግ የክለቦች የሴካፋ ውድድር የደቡብ አፍሪካው ክለብ ሱፐር ስፖርት ሰዎች አዩኝ። የአሁኑ የአል አህሊ አሠልጣኝ ሞሴማኒ በጊዜው የሱፐር ስፖርት አሠልጣኝ ነበር። እንደምታውቁት በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ከሚገኙ ትላልቅ አሠልጣኞች አንዱ ነው። በጊዜውም ራሱ መጥቶ ነበር ኮንትራት እንድፈርን ሲያግባባኝ የነበረው። ግን ሚቾ አሁንም ከዚህ የተሻለ ክለብ መሄድ ትችላለህ ብሎ ሀሳቡን አልተቀበለውም ነበር። ያው በጊዜው ሱፐር ስፖርት በጣም ትልቅ ክለብ ሳይሆን መሐከለኛ ክለብ ነበር። እኔም በድጋሜ በሚቾ ምክር እጄ ላይ የነበረውን ኮንትራት ውድቅ አደረኩት። እኔም በራሴ እተማመን ነበር። ይህ አለፈና በዓመቱ መጨረሻ ከሌላኛው የደቡብ አፍሪካው ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ጥያቄ መጣ። በደቡብ አፍሪካ ትልቁ ክለብ ስለነበረም ሚቾ ይሄንን ነው ላንተ የምፈልገው አለኝ። እኔም እሺ ብዬ 1999 ወደ ኦርላንዶ ፓየሬትስ ሄድኩ። ከዛም በኋላ እስካሁን ወደ ሀገሬ አልተመለስኩም።

ከዛስ?

እንደምታውቀው በአፍሪካ፣ ኤዢያ እና አውሮፓ የሚገኙ ክለቦች እየተዟዟርኩ ተጫውቻለሁ። ከደቡን አፍሪካ ቆይታዬ በመቀጠል ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ነው ያመራሁት። ከዛም ፊንላንድ፣ ቬትናም፣ ባንግላዲሽ፣ ማሌዢያ እና ህንድ አምርቻለሁ። በእነዚ ሀገራት በተለያዩ ክለቦች ተጫውቻለሁ።

በእግርኳስ ህይወትህ በበርካታ ክለቦች ተጫውተሃል። ከዚህ መነሻነት ፍቅሩ ተፈራ በአንድ ክለብ ተረጋግቶ መቆየት አይችልም ይባላል። ይህ ከምን የመጣ ነው?

ችግር አይደለም። እኔ ደስተኛ የምሆንበትን ነገር ነው የምፈልገው። ምክንያቱም መጀመሪያ እኔ ተደስቼ ነው በኳስ ሰውን የማስደስተው። የሚባለው ነገር ከገንዘብ ጋር ተያይዞም አይደለም። በምሄድበት ክለብ ጥሩ ገንዘብ ይከፈለኛል። ግን አለመስማማቶች ሲመጡ ወደ ሌላ ነገር ውስጥ ከመግባት አማራጮችን አያለሁ። ወደየትኛውም ክለብ ስገባ አራት እና አምስት ክለቦች ይጠይቁኛል። ገና በአንድ ክለብ በግማሽ አመቴም የሚጠይቁኝ ክለቦች ይኖራሉ። እኔ የምመርጠው ደስተኛ የሚያደርገኝን ክለብ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ልምዱን ስለምፈለግ እና ወደፊት ወደ ሀገሬ ተመልሽ በየሀገሩ ያለውን ልምድ ለታዳጊዎች ለማካፈል ስለምፈልግ ነው። በዋናነት ግን የሚያስደስተኝን ክለብ ለመፈለግ ነው። እንጂ ችግር ኖሮብኝ አይደለም።

በእግርኳስ የክለብ ህይወትህ ባሳካው ኖሮ ብለህ የምታስበው ነገር ይኖራል? ወይም የሚቆጭህ ነገር?

የተለያዩ ሀገራትን ተመልክቻለሁ። አውሮፓም ብዙ ሀገር አይቻለሁ። ለዝግጅትም የምንሄድባቸው ሀገራት ነበሩ። ለምሳሌ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ኦስትሪያም ተጉዣለሁ። አንድ ግን በእንግሊዝ የታችኛው የሊግ እርከን የሚወዳደረው ጂሊንግሀም ያጋጠመኝ ነገር ነበር። ይህ የጠቀስኩት ክለብ ፈልጎኝ ሄጄ ነበር። ፓስፖርቴንም ወስደው የሥራ ፈቃድ እንዳገኝ ጥረው ነበር። ግን በፊፋ እና በእንግሊዝ ባለ ህግ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል። እና ይህ ሁሌ ይቆጨኛል። አሁንም እኔ በእንግሊዝ መጫወት ባልችልም ሌላ የሀገሬ ልጅ ሄዶ እንዲጫወት እመኛለሁ። እንዳልኩት እኔ ባይሳካልኝም እዚሁ ከሀገራችን የወጣ ተጫዋች ሄዶ እንዲጫወት እፈልጋለሁ።

በእግርኳስ ህይወትህ ከየትኞቹ ትላልቅ ተጫዋቾች ጋር ተጫውተሃል. . .

ልክ ነው። ከበርካታ ስመ ጥር ተጫዋቺች ጋር የመጫወት ዕድል አግኝቻለሁ። ለምሳሌ ከነዴልፒየሮ፣ ማታራዚ፣ ፔሬዝ፣ ሊዩምበርግ፣ ሊዊስ ጋርሲያ ጋር ተጫውቻለሁ። በተጨማሪም ከተለያዩ የአፍሪካ ታዋቂ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቻለሁ። ቅድም እንዳልኩት በተለያዩ ክለቦች ስለተጫወትኩ ከበርካቶች ጋር ተገናኝቻለሁ። በክለቦቹም በግሌ የተለያዩ ክብሮችን አግኝቻለሁ። በዚህ አጋጣሚ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። ወደፊት ከእኔ የተሻለ ወደ ውጪ የሚወጡ ተጫዋቾች ሀገራችን ይኖሯታል ብዬ አስባለሁ።።


ከዚሁ ጋር በተያያዘ አብረሀቸው ከተጫወትካቸው ተጫዋቾች ማንን ታደንቃለህ?
ስለማድነቅ ቅድም ያልኩህ ነው። ግን በብሔራዊ ቡድን ሙሉዓለም ረጋሳ እና አሸናፊ ግርማ በጣም ጠቅመውኛል። የሁለቱም ብቃት ለእንደ እኔ አይነቱ የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሚጠቅም ነው። ሩዋንዳ ላይ በሴካፋ ውድድር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ስሆም ካገባኋቸው ጎሎች ግማሹ በእነሱ ኳሶች ነው። አሸናፊም የረጅም ጨዋታው በጣም አስደናቂ ነው። እንደውም ከኢትዮጵያ ወጥተው መጫወት ከነበረባቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። እና አብረውኝ ከተጫወቱት የሁለቱን ብቃት አደንቃለሁ።

ከማድነቅ ጋር በተገናኘ ካሰለጠኑህ አሠልጣኞችስ ማንን ታደንቃለህ?

እንደምታውቀው ሀገር ውስጥ ብዙ አልቆየሁም። ከምሰማው ነገር ተነስቼ ደግሞ መምረጥ ይከብደኛል። ስለዚህ ካየኋቸው አሠልጣኞች በብሔራዊ ቡድን ከአሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጋር ሰርቻለሁ። አንዳንዶቹ እንደውም አንድ አይነት ባህሪ አላችሁ ይሉናል። እኔ በእሱ ባህሪ ደስተኛ ነኝ። የእሱ አይነት ባህሪ የበለጠ ቢኖረኝ እንደውም ከዚህ የበለጠ እደርስ ነበር። ግን የእሱን ባህሪ በጣም ነበር የምቀበለወ። በዚሁ አጋጣሚ እንደውም ሴካፋ ልንሄድ ብለን ልምምድ ላይ በጣም አስደናቂ ብቃቴን እያሳየሁ ውድድሩ ሊጀመር አንድ ሳምንት ሲቀረው አውቶብስ ላይ እግሬን ዘርግቼ ስሄድ በአጋጣሚ ያልታሰበ ጉዳት አጋጠመኝ። አሥራት በጣም ትልቅ ቦታ እንደምደርስ ሁሌ ይነግረኝ ስለነበር በእኔ እምነት ነበረው። በወቅቱ በአጥቂ ቦታ ከሰባት በላይ ተጫዋቾች ነበሩ። ግን አስራት ለእኔ የሁለት ቀን እረፍት ሰጠኝ እና በአቋም መፈረሻ ጨዋታ መዳኔን ካወቀ በኋላ አስገባኝ። የሚገርምህ በ20 ደቂቃ ውስጥ እኔ ሁለት ጎል አገባሁ። ከዛ ወዲያው ተቀይሬ እንድወጣ አደረገኝ። እኔ ደንግጬ ነበር። ግን እሱ በቃ አምኜብሀለው ብሎ ነበር ያሶጣኝ። ከአሠልጣኝ እንደዚህ አይነት እምነት ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ መነሻነት ከሀገር ውስጥ አሥራት ኃይሌን አደንቃለሁ። ከውጪ ደግሞ እነሚቾን አደንቃለሁ።

በኢትዮጵያ ቆይታህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫዎችን እንዲያገኝ ግቦችን እያስቆጠርክ ግልጋሎት ሰጥተሃል። አንድ ጨዋታ ላይ ደግሞ የግብ ዘብም ሆነህ ነበር። ግብ ጠባቂ ሆነህ የተጫወትክበትን ጨዋታ በደንብ ታስታውሰዋለህ?

እውነት ለመናገር በደንብ አላስታውሰውም (እየሳቀ)። ረዘም ያለ ዓመት ስለሆነም ከማን ጋር ስንጫወት እንደነበር ላስታውስ አልቻልኩም። እኔ ሁለገብ ለመሆን ልምምድ ላይ እሰራለሁ። በጊዜው ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ ይወጣብናል። እንዳልኩት ከዋናው ልምምድ በኋላ እንደ ቀልድ ግብ ጠባቂ ሆኜ እለማመድ ሰልነበር ልክ በረኛችን በቀይ ሲወጣ እኔ ግብ ጠባቂ እንድሆን ትዕዛዝ ተሰጠኝ። ትዕዛዙንም ተቀብዬ ጨዋታውን በግብ ጠባቂነት ጨርሻለሁ። በነገራችን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁ ብቻ ሳይሆን ደቡብ አፍሪካ ሱፐር ስፖርት እያለሁም አንድ ጊዜ ግብ ጠባቂ ሆኜ ተጫውቻለሁ።

ፍቅሩ! ከብሔራዊ ቡድን ጋር የተያያዘ ጥያቄ ደግሞ ላቅርብልህ። ብዙዎች ሀገርህን በደንብ ያላገለገልክበትን ምክንያት መስማት ይፈልጋሉ። በተለይ ደግሞ 2013 ላይ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያመራ አልነበርክም። ለምንድን ነው በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ያልተጫወትከው?

ከተመረጥኩበት ጊዜ ጀምሮ ወደ አስር ዓመት ሀገሬን አገልግያለሁ። በሴካፋ ውድድር ላይም ሻምፒዮንም ሆኟለሁ። ይህ ደግሞ ትልቅ ነገር ይመስለኛል ከሀገርህ ጋር ዋንጫ ማንሳት። ከዚህ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ መጫወት የነበረብኝ ነገር ነበር። ግን አልሆነም። እኔ እግዚአብሔር አልፈቀደም ነው የምለው። ለምን አልሆነም ብዬ የምፀፀትበት ምክንያት ምንም የለም። ሁሉም ለበጎ ነው ብዬ አልፌዋለሁ።

ዘለግ ያሉ ዓመታትን በተለያዩ ሀገራት ተጫውተህ ካሳለፍክ በኋላ ለምን ወደ ሀገርህ አልተመለስክም?

አንዳንድ ክለቦች ጠይቀውኝ ነበር። በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ጥምር ሚና እንዳገለግላቸው የፈለጉ ነበሩ። ግን በጠየቁኝ ክለብ ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞች ያለኝ ልምድ እና ግርማ ሞገስ ያስፈራቸዋል መሰለኝ ወደ ኋላ ማለት ጀመሩ። በዚህ አጋጣሚ ማለት የምፈልገው ነገር ትክክለኛ ስራ የሚሰራ አሰልጣኝ የሚፈራ አይመስለኝም። የፈለገ ነገር ቢኖር ዋናው መማማራ ነው። ግን በዚህ ምክንያት ነገሮች ሳይሳኩ ቀሩ። በሌላ ሀገር ቢሆን እንደእኔ ልምድ ያለው ሰው ተለምኖ ነበር የሚሰራው። ግን እኛ ሀገር ይህ ገና አልተለመደም። አልተለመደም ብለን ግን ዝም ማለት የለብንም። አሁን ላይ ተጫዋቾች ልምድ የሚሰጣቸው እና የሚያማክራቸው ሰው ከጎናቸው ይፈልጋሉ። እኔ ደግሞ ልምዴን በመናገር መስጠት ብቻ ሳይሆን አብሬያቸውን እየተጫወትኩ ያለኝን ለማካፈል ዝግጁ ነን። እንደምታየኝ በሁሉ ነገር ብቁ ነኝ። ራሴን በጣም ነው የምጠብቀው። ለዚህም ነው አሁን ድረስ እንደዚህ ብቁ የሆንኩት። ይህንን ልምድ ደግሞ ለተጫዋቾች ማካፈል እፈልጋለሁ። አሁንም ይህንን የሚፈልጉ ክለቦች አሉ። ከተሳካ ምናልባት በዚህ ዘርፍ በሀገሬ ክለብ ልትመለከቱኝ ትችላላችሁ። በዋናነት መጫወቱ ላይ ሳይሆን ልምዴን ማካፈሉ ላይ ነው ሀሳቤ። እንደምታቁት ወደ 18 ዓመታት ተጫውቻለሁ። 18 ዓመታትን በወጥነት ዝግጁ ሆነህ እንዴት መጫወት ትችላለህ የሚለውን ነው ማሳየት የምፈልገው። እርግጥ አሁንም ድረስ ለምን አትጫወትም የሚል ነገር ሰዎች ይነሳሉ። ይህንን ሲሉኝ እኔ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ከድሮ ጀምሮ ወፈር ብዬ መታየት ስለማልፈልግ ይህንን ስባል ደስ ይለኛል። በአጠቃላይ ከተጫዋቾች ጎን ሆኜ እኔ የሚሰማኝን እና በወጥነት ይህንን ሁሉ ዓመት ያገለገልኩበትን ልምድ ለማካፈል በአሠልጣኝ ቡድን ውስጥ ለመግባት ነው እንቅስቃሴዬ እና ፍራጎቴ።

ፍቅሩ መቼስ በርካታ ድንቅ ድንቅ ኳሶችን ከመረብ አሳርፈካል። በራስህ ልብ ውስጥ የቀረች ያስቆጠርካት ጎል የቷ ነች?

በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ምርጥ ምርጥ ጎሎችን አስቆጥሬያለሁ። በርከት ያሉ የመቀስ ምት ጎሎችም አሉኝ። ብዙዎቹ አክሮባቲክ ስለሆንክ ነው ብዙ የመቀስ ምት ጎል የምታገባው ይላሉ። ልክ ነው እኔ አክሮባት እሰራ ነበር። ይህ እንደውም በእግርኳስ ህይወቴ ጠቅሞኛል። ወደ ጥያቄህ ስመለስ በርካት አሉ። እኔ ራሱ አሁን ላይ ቁጭ ስል የማያቸው የበፊት ጎሎቼ አሉ። የማያቸው ጎሎች ላይ ስሜቶች አሉኝ። እኔ በግሌ ይሄኛው ብዬ መምረጥ ይከብደኛል። ህዝቡ የሚፈልገውን ይምረጥ።

ቅድም በአሠልጣኝ ቡድን አባላት ውስጥ በረዳትነት ለመግባት እንቅስቃሴ ላይ ነኝ ብለኸኛል። በአሠልጣኝነት ብቅ ለማለት ምን ያህል ራስህን እያዘጋጀህ ነው?

የአሠልጣኝነት ስልጠናዎችን እየወሰድኩ ነው። የዩ ኤ ፋ ሲ ላይሰንስም አለኝ። በኮቪድ ምክንያት ተጓተተ እንጂ ወደ ስኮትላንድ ሄጄ የዩ ኤ ፋ ቢ ላይሰንስ የምወስድበትንም ዕድል አግኝቼ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የካፍ ሲ ላይሰንስ አለኝ። የቢ’ውንም ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ። ኢትዮጵያም ሆነ ደቡብ አፍሪካ ከመጣ እወስዳለሁ። እኔ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ደቡብ አፍሪካ ላይም ከኢንስትራክተሮች ጋር እንገናኛለን። ስልጠናዎች ሲመጡ ይነግሩኛል። ምንም ቢሆን ደግሞ እየሰራሁም ራሴን አሳድጋለሁ። ለዛም ነው በረዳት አሠልጣኝነት ለመስራት የምፈልገው። አንደኛ ከሀገሬ ሰዎች ጋር መስራት እፈልጋለሁ። ልምዶችንም መቀያየር እፈልጋለሁ። ስለዚህ በረዳት አሠልጣኝነት ለማገልገል ፍላጎቱ አለኝ። ዝግጁም ነኝ።

ፍቅሩ ሚዲያ ላይ ብዙ አትታይም። የስፖርት ቤተሰቡ ደግሞ ስላንተ ብዙ ማወቅ ይፈልጋል። በተለይ ስለ አኗኗርህ። የኑሮ ዘይቤህ ምን ይመስላል?

ከድሮም ጀምሮ የእኔ የአኗኗር ዘይቤ ቀለል ያለ ነው። ሁሌ ከአምሮዬ የማይጠፋ ነገር አለ። እርሱም ታዋቂነት ቢመጣም መውረድ በየሆነ አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል የሚለው ነው። ህይወቴን በሙሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ ነው የምኖረው። ከድሮ ጀምሮ የነበሩኝ ጓደኞቼ አሁንም ድረስ አብረን ነን። እንደ በፊቱ ሰፈር ውስጥ ድንጋይ ላይም ቁጭ ብለን እናወራለን። ሰው በቴሌቪዥን ሲያየኝ እንደዚህ አይመስለውም። ግን እኔ በፊት ሰፈር ውስጥ የማሳልፈውን አሁንም አደርገዋለሁ። ይህም በጣም ነው የሚያስደስተኝ። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ጊዜ አሳልግ ነበር። በተለይ አየር ጤና የሚገኘው አቡነ አራጋይ ቤተክርስቲያን አሁን ድረስ እየሄድኩ ቁጭ እላለሁ። እዛም እየሄድኩ መንፈሴን አሳድሳለሁ። በአጠቃላይ ቀላል ኑሮ ነው ያለኝ። ከማንም ጋር ተቀላቅዬ መግባባት እችላለሁ። ያንን ሁላ ታሪክ በሰው ሀገር ሄጄ ብሰራም ሁሉም ነገር ከንቱ እንደሆነ አቃለሁ። ስለዚህ ቀለል ያለ ህይወት ነው የምኖረው።

ብዙዎች ስላንተ ሲያስቡ የራስ መተማመንህን ያነሳሉ። ይህንን እኔም እጋራለሁ። የሚገርም የራስ መተማመን ነው ያለህ። ይህ ከምን የመጣ ነው? እንዴትስ አዳበርከው?

ልክ ነው። ይሄንን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆን በየሄድኩባቸው ሀገራትም ያሉ ሰዎች ይሉታል። ይህ የተፈጥሮ ጉዳይ ይመስለኛል። ነገሮችን ለማሳካት ብዙ ነገር እሞክራለሁ። ግን ባይሳኩም ምንም አይመስለኝም። ቅድም እንዳልኩህ ቤተ-ክርስቲያን ማደጌን የጠቀመኝ ይመስለኛል። ሁሉ ነገር ፈጣሪ ሲፈቅድ ነው የሚሆነው ብዬ አምናለሁ። ይሄም ነው ልቦናዬን ጠንካራ አድርጎት ወደፊት እንድጓዝ ያደረገኝ። በስራዬ ላይ ማድረግ አለብኝ ያልኩትን ነገር አደርጋለሁ። ይህ ባህሪዬ ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጣ አስቸጋሪ ነው ተብሎ ነው የሚተረጎመው። ውጪ ግን ክለቦቼም ሆነ አሠልጣኞቼ በጣም ነው የሚፈልጉት። ይህ አስተሳሰብ በሀገራችን ቢቀየር ጥሩ ይመስለኛል። እኔ ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ በጣም ትልቅ የራስ መተማመን አለኝ።

 
የግል ህይወትህስ ምን ይመስላል?

አራት ልጆች አሉኝ። ሁለት ወንድ ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ። ትልቁ ነገር ልጅ ማፍራት ነው። እግዚአብሔር ይመስገን ይህንን አሳክቻለሁ።

ከዚሁ ከግል ህይወት ጋር በተያያዘ በጣም ያዘንክበት አጋጣሚ አለ?

ሰዎች ነን እናዝናለን። በተለይ ደግሞ እናት እና አባቴን ባጣሁበት ጊዜ በጣም አዝኛለሁ። አሁን ላይ የደረስኩበትን ደረጃ ቢያዩ እላለሁ። ግን እግዚአብሔር አልፈቀደም። እኔ ጠንካራ አምሮ ስላለኝ የትም ቦታ የምሰራውን ስራ እነሱ ያዩታል ብዬ አስባለሁ።

ፍቅሩ ተፈራ አሁን ምን ላይ ነው የሚገኘው? በምን ዙርያ እየተንቀሳቀስክ ነው?

ሁሉም ነገር ሲያልቅ ነው መናገር የምፈልገው። አንዳንድ ነገሮች እየሞከርካቸው የሚሳኩበት ጊዜ ሊራዘም ይችላል። ግን እርግጠኛ ነኝ ሙሉ ለሙሉ ይሳካልኛል። በጨረፍታ ለመንገር በፊት የነበርኩባቸው ክለቦች የእኛን ሀገር ታዳጊዎች ለማውጣት በስሜ ፕሮጀክት እዚህ ሊከፍቱ ነው። ፈጣሪ ከፈቀደ በእኔ ፕሮጀክት ታዳጊዎች ወደ ውጪ የሚወጡበትን ነገር ለመዘርጋት እየጣርን ነው። አሁን ላይ በኮቪድ ምክንያት ጉዳዩ ትንሽ ተንጓቷል።

እየጨረስን ነው። ስለ ሀገራችን እግርኳስ የሆነ ነገር ብትለኝ ደስ ይለኛል። የኢትዮጵያ እግርኳስ በፍቅሩ እይታ ምን ይመስላል?

ሁሌ እንደሚባለው ከታዳጊዎች ጀምሮ በሀገራችን መሰራት አለበት። እኛ ሀገር ብዙ የአጭር ጊዜ እቅድ ነው ያለው። ሰውን በተፈጥሮ ብታየው ገና እንደተወለደ ተነስቶ አይሮጥም። ቀስ እያለ ዳዴ እያለ ነው እየተማረ የሚሄደው። በእኛ ሀገረ እግርኳስ ግን እንዳልኩሁ ሁሉም አሁን ካልሆነ የሚል ነው። የረጅም ጊዜ እቅድ የለንም። ክለቦችም ዓላማ ይዘው አይደለም የሚንቀሳቀሱት። እንደምታስታውሰው በቅርቡ ነው ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፍነው። አሁን ደግሞ ፈጥኖልን በስምንት ዓመታችን አልፈናል። በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች የመታየቱን ዕድል አግኝተዋል ግን መታሰብ ያለበት ቀጣዩስ የሚለው ነው። እዚሁ ላይ ደግሞ እንዴት ነው የምድብ ጨዋታዎችን አሸንፈን የምናልፈው የሚለውን ማሰብ ያስፈልገናል። በዋናነት ግን ሌሎቹ ሀገራት የሚከተሉትን የረጅም ጊዜ እቅድ መከተል ያስፈልገናል። ሌሎቹ ሀገራት ለረጅም ጊዜ ተፎካካሪ የሚሆኑትም ለዚህ ነው። እኛ አይደለም የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ውድድርን ዋንጫ ካገኘን እንኳን ዓመታት ተቆጥረዋል። ስለዚህ በሙያተኛ ማመን እና ሙያተኛውን ማሰራት ያስፈልገናል። በእኔ እይታ ኳስ ያልተጫወተ ሰው በወረቀት ብቻ ታዳጊዎችን ማሰራት የሚችል አይመስለኝም። ታዳጊዎችን ስታሰራ ራስህ እያሳየህ ካልሆነ አይቻልም።

በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገው ሰው ካለ ዕድሉን ልስጥህ እና ቆይታችንን እናገባድ?

መጀመሪያ ማመስገን የምፈልገው ፈጣሪዬን ነው። እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እኔ ተግቼ ሰርቼ ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት። የእኔ ጥረት እንዳለ ሆኖ መግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ብዙ ሰዎች ያበረታቱኝ ነበር። እነሱንም አመሰግናለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ ወንድሞቼን ከምንም በላይ ማመስገን እወዳለሁ። በአጠቃላይ ጓደኞቼን እና የሰፈሬ ልጆችንም አመሰግናለሁ።

 

ፍቅሩ ዛሬ በተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ላይ ለጨዋታው ኮከብ ፀጋዬ መላኩ ሽልማት ሲያበረክት