የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ.ማ ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ጋር በመተባበር ለአስራ ስድስቱ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ያዘጋጀው ስልጠና በይፋ ተጀምሯል።
የፕሪምየር ሊጉን አሰልጣኞች አቅም እና ዕውቀት ለማሳደግ የተለያዩ የማሻሻያ ሥልጠናዎችን ለማዘጋጀት የሊጉ አክስዮን ማኅበር ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ጋር አስቀድሞ በገባው ስምምነት መሠረት ስልጠናው ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው በዚህ ይፋዊ የስልጠና ጅማሮ ፕሮግራም ላይም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፥ የሊግ ካፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፋ እና የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኔ ዋልተንጉሥ እንዲሁም በዲኤስቲቪ በኩል ወ/ሮ ሰሎሜ ናይዶ በክብር እንግድነት ታድመዋል።
ከመልቲቾይዝ እና ከሆላንድ እግርኳስ ማኅበር (KNVB) የመጡ ሦስት አሰልጣኞች ሮጀር ሾውናር (ከሆላንድ)፥ ፍራንሲስ ይላውዚ (ከኬንያ) እና ሬይሞሆ ናሮታ (ደቡብ አፍሪካ) ስልጠናውን የሚሰጡ ሲሆን የፕሪምየር ሊጉን አሰልጣኞች አቅም ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሻግራል ተብሎም ታምኖበታል። ስልጠናው ለአምስት ቀናት በሚኖረው ቆይታ የንድፈ ሀሳብ ትምህርቱ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ሲከወን የተግባር ትምህርቱ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሚካሄድ ይሆናል።
ለአምስት ቀን ማርዮት ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ ስልጠናውን ይካፈላሉ ተብለው ከሚጠበቁ አስራ ስድስቱ አሰልጣኞች መካከል አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ፥ አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት እና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ላይ ያልተገኙ መሆናቸውን ተመልክተናል። ይህ ስልጠና ከተጠናቀቀ በኃላ ከጥቅምት ሁለት ጀምሮ ደግሞ ለሠላሳ ስድስት ምክትል አሰልጣኞች ስልጠናውን የሚወስዱ ይሆናል። በዛሬው የንድፈ ሀሳብ ትምህርት በዋናነት ከሀገራችን እግርኳስ አኳያ ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት እና የሰልጣኞቹን የሥራ ልምዶች እና የእግርኳስ ህይወትን መሠረት ያደረገ ነበር።
በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ የተነሱ ሌሎች ዓበይት ጉዳዮችን ከቆይታ በኃላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።