በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በተዘጋጀው የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ስልጠና ወቅት አቶ ኢሳይያስ ጂራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞችን አቅም እና ዕውቀት ለማሳደግ የሊጉ አክስዮን ማኅበር ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ጋር በመተባበር ለአምስት ቀናት የሚቆየው ስልጠና ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ አግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል።
” ከሁሉ አስቀድሜ ይህን የስልጠና መድረክ ያዘጋጀውን አካል አመስግኜ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት እፈልጋለሁ። የሊጋችን መመስረት ውጤቱ እንደነዚህ ያሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ነው። አንድ መልካም ነገር ሲሰራ ሌላ መልካም ነገር ይዞ ነው የሚመጣው። ይህ ስልጠና ላይሰንስን መሠረት ያደረገ አይደለም። መታወቅ ያለበት ከአሁኑ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሆኑን ነው። ብዙ እንዲህ ያለ ስልጠናዎች ሲሰጡ ጆሮው የሚቆም ብዙ አሰልጣኞች ከውጭ ቆመው የሚጠብቁ አሉ። ለዓመታት ስልጠና ሳይሰጥ የቀረ በመሆኑ። አሁን የ ዲ ላይሰንስ መስጠት ጀምረናል። በመቀጠል ለስድስት ዓመት ተቋርጦ የቆየውን የስልጠና መንገዳችን የ ሲ ላይሰንስ ከዛም በየደረጃው የቢ እና የ ኤ ላይሰንስ የሚሰጥ ይሆናል። በመቀጠል ፕሮፌሽናል ስልጠናዎች የሚሰጡ ይሆናል። የዛሬው ስልጠና በተለየ ሁኔታ ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የተዘጋጀ ነው።
” ሁልጊዜ ጎል እየቆጠርን መውጣት የለብንም። እግርኳሱ እንዲያድግ የምንፈልግ ከሆነ በዕውቀት የሚያሰለጥን የሚመራ ሰው ያስፈልጋል። ስልጠናችን ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆን አለበት። ከዚህ ወጥተን ትርጉም ወዳለው ስልጠና ለመግባት ደግሞ እዚህ ቁጥራችሁ አነስተኛ የሆነ ግን የሥራው ባለቤት የሆናችሁ አሰልጣኞች ናችሁ እዚህ ያላችሁት። የሀገሪቱ እግርኳስ እናንተ እጅ ላይ ነው ያለው። እግርኳሱን መለወጥ ካለባቹሁ እናንተ ናችሁ። ስለዚህ ይህ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባችሁ አውቃችሁ ስልጠናውን በትኩረት እንድትከታተሉ አደራ እላለሁ። ወደፊትም አንዲህ ያለ አቅም ግንባታ ላይ መሠረት ያደረጉ ስልጠናዎች መስጠት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። ብለዋል።