በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥሙት ደቡብ አፍሪካዎች ለወሳኞቹ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ልምምድ መስራት ሲጀምሩ ሁለት ተጫዋቾችንም ቀንሰው አዲስ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ጋና እና ዚምባቡዌ በሚገኙበት ምድብ ሰባት የተደለደሉት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ መስከረም 29 እና ጥቅምት 2 የዓለም ዋንጫ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን እርስ በእርስ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና ኤፍ ኤን ቢ ስታዲየም የሚያከናውኑ ይሆናል። ለእነዚህ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎችም የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሁጎ ብሮስ ከቀናቶች በፊት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበው ነበር። ተጫዋቾቹም በትናንትናው ዕለት ከተሰባሰቡ በኋላ ዛሬ ልምምድ መስራት ጀምረዋል።
ብሔራዊ ቡድኑም 14500 ተመልካቾችን በሚይዘው በዶብሶንቪል ስታዲየም የመጀመሪያ ልምምዱን መስራቱ ተጠቁሟል። አሠልጣኙ በቅድሚያ ከጠሯቸው 23 ተጫዋቾች ውስጥ ከማሚሎዲ ሰንዳውንስ የተመረጠው ተከላካዩ ሞሳ ሌቡሳ በጉዳት እንዲሁም ከኦርላንዶ ፓየሬትስ የተመረጠው አማካዩ ጉድማን ሞስሌ የደረሰውን ጥሪ ሳይቀበል በመቅረቱ ከስብስቡ ውጪ መሆናቸው ታውቋል። በእነሱ ምትክ ደግሞ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጫወት ጥሪ የቀረበለት የሱፐር ስፖርቱ የመሐል ተከላካይ ሉክ ፍሉርስ እና ጄሴ ዶን በአዲስ መልክ ጥሪ ቀርቦላቸው ስብስቡን መቀላቀላቸው ተጠቁሟል።
በተያያዘ ዜና ጥቅምት 2 በኤፍ ኤን ቢ ስታዲየም ዋልያውን የሚያስተናግደው ብሔራዊ ቡድኑም በስታዲየሙ ደጋፊዎችን እንደሚያገኝ ተሰምቷል። በዚህም የደቡብ አፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ከአራት ቀናት በኋላ በጋራ በሚሰጡት መግለጫ ዝርዝር ጉዳዮች እንደሚብራሩ ቢጠቆምም የደቡብ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጨዋታ እንደ ሙከራ ፕሮጀክት (Pilot project) ተወስዶ የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱ ደጋፊዎችን ብቻ ወደ ስታዲየም ለማስገባት መወሰኑ ተጠቁሟል።