ከቀናት በኋላ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ተጫዋች በጉዳት ቀንሶ ልምምዱንም አጠናክሮ ቀጥሏል።
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በአህጉሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መስከረም 29 እና ጥቅምት 2 በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታውን ያደርጋል። ለሁለቱ ወሳኝ ጨዋታዎች ይረዳቸው ዘንድ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ታፈሠ ሰለሞንን በዲሲፕሊን ምክንያት ቀንሰው በምትኩ በዛብህ መለዮን በመጥራት ዝግጅታቸውን ከ መስከረም 15 ጀምሮ ባህር ዳር ማድረግ ጀምረዋል።
ዋና አሠልጣኙ ቀድመው ከጠሯቸው ተጫዋቾች መካከል ስድስቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በሰዓቱ ባያገኙም ከአንድ ቀን የልምምድ መርሐ-ግብር በኋላ ተጫዋቾቹን በማግኘት በተሟላ ሁኔታ በቀን አንድ ጊዜ በዋናው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና የመለማመጃ ሜዳ ሲሰሩ ነበር። በትናንትናው ዕለት እረፍት የተሰጣቸው ተጫዋቾቹም አመሻሽ ላይ ምክትል አምበላቸው የሆነውን እና ብቸኛው ከሀገር ውጪ የሚጫወተውን ሽመልስ በቀለን ማግኘታቸው ታውቋል። በግቡፁ ክለብ ኤል-ጎውና የሚጫወተው ተጫዋቹም አመሻሽ ላይ አጋሮቹን ባህር ዳር ብሉ ናይል (አቫንቲ) ሆቴል ከተቀላቀለ በኋላም በዛሬው የቡድኑ ልምምድ ላይ መሳተፉ ተጠቁሟል።
ከረፋድ 4:45 ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመለማመጃ ሜዳ በተከናወነው የቡድኑ የዛሬ የልምምድ መርሐ-ግብር ለ120 ደቂቃዎች የቆየ ነበር። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቹም በአብዛኛው በጠባብ ቦታዎች ኳስ ቅብብልን መሠረት ያደረጉ ልምምዶች ሲያሰሩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በግማሽ ሜዳ ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የእርስ በእርስ ጨዋታ አድርጓል።
ከሁለት ቀናት በፊት መጠነኛ ጉዳት (እግሩ ላይ በተፈጠረ ቁስል) አጋጥሞት የነበረው የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል በዛሬው ልምምድ በሙሉ አቅሙ መሳተፉ ተጠቁሟል። ሌላኛው የቁርጭምጭሚት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው የመስመር ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ ግን ለጨዋታዎቹ በቶሎ ዝግጁ እንደማይሆን መታወቁን ተከትሎ ከስብስቡ ውጪ እንደሆነ ቀትር ላይ ማስነበባችን ይታወቃል።