ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ| ሰበታ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ሰበታ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት ተከታታይ ድል ሲያስመዘግብ ለውድድሩ አሸናፊነትም ተቃርቧል፡፡

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ 4፡00 ሰዓት ሲል ድሬዳዋ ከተማን ከ ሰበታ ከተማ አገናኝቷል፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ ለሰበታ ከተማ ደግሞ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው ሦስተኛ ሆኖ የተመዘገበለት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ ጥቂት ሙከራዎች እና የሰበታ ከተማ ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድ ጎልቶ በታየበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱ ቡድኖች አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ አመዝነው በቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስን አልመው የገቡ ቢመስሉም የድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች የአቋቋም ስህተት በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት ለሚጫወቱት ሰበታ ከተማዎች አመቺ ሆኖላቸው ቀርቧል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያው አምስት ደቂቃ ላይ የድሬዳው ወጣቱ አጥቂ ሳሙኤል ዘሪሁን ከመስመር የተሻማለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በወጣችበት ሙከራ ቀዳሚውን አጋጣሚ መመልከት ችለናል፡፡ ከእንቅስቃሴ ባሻገር የሚባክኑ ኳሶች በበዙበት በዚህኛው አጋማሽ የጨዋታው ደቂቃ እስኪጋመስ ድረስ በተወሰነ መልኩ ድሬዳዎች በማማዱ ሲዲቤ እና ሳሙኤል ዘሪሁን አማካኝነት ሙከራን አድርገዋል፡፡ በተለይ 25ኛው ደቂቃ ላይ ማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ በሰበታ የግብ ትይዩ መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ሳሙኤል ዘሪሁን ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ምንተስኖት አሎ በሚገርም ብቃት አድኖበታል፡፡

 

31ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች የድሬዳዋ ተከላካዮች የሰሩት ስህተት በመጠቀም ግብ አግኝተዋል። በኃይሉ ግርማ በድሬዳዋ ተከላካዮች መሀል ያሳለፈለት ኳስ የተከላካዩ ሚኪያስ ካሳሁን ስህተት ታክሎበት የፍሬው ጌታሁን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ ናሚቢያዊው አጥቂ የቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሯል፡፡ጎል ካገኙ በኋላ ይበልጥ ንቃት የተስተዋለባቸው ሰበታዎች ዘላለም ኢሳያስ ከርቀት ካደረጋት ሙከራ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማለትም 40ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ሳሙኤል ሳሊሶ በሚያስደንቅ እይታ ነፃ ሆኖ ለነበረው ጂኒያስ ናንጄቤ ሰጥቶት ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡

ከዕረፍት መልስ ግብ ማስቆጠር የተሳነው ድሬዳዋ ከተማ አከታትሎ የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ የተወሰነ ጥረት ሲያደርግ ብንመለከትም የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች የሚሰሩት ተደጋጋሚ ስህተት ግን ለፈጣኖቹ የሰበታ አጥቂዎች ያመቹ ሆነው ታይተዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው ሱራፌል ጌታቸው የግል አቅሙን በመጠቀም የሰጠውን ኳስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ሳሙኤል ዘሪሁን ለድሬዳዋ አስቆጠረ ሲባል ባመከናት አጋጣሚ በዚህኛው አጋማሽ ቀዳሚዎቹ የግብ ዕድል ፈጣሪዎች ሆነዋል፡፡ የመልሶ ማጥቃትን በሂደት እየተጠቀሙ መምጣት የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች በ60ኛው ደቂቃ ጌቱ ኃይለማርያም ከመስመር አሻምቶ ፍፁም ገብረማርያም በግንባር ክፍት የግብ ማግባት አጋጣሚን ቢያገኝም አልተጠቀመበትም፡፡

65ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተስፋዬ በግብ ክልል ውስጥ በሙህዲን ሙሳ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ ከገባ በሜዳ ላይ ሁለት ደቂቃ የቆየው ሙኸዲን ጎል አስቆጥሮ ድሬዳዋን 2-1 አሸጋግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ወጣቱ አጥቂ መሀመድ አበራ የድሬዳዋን የተከላካይ መስመር ስህተት በደንብ መጠቀሙን ያረጋገጠች ሦስተኛ ግብ ከመረብ አሳርፎ ሰበታ ከተማ ወደ 3-1 ውጤት ተሸጋግሯል፡፡ ተቀይሮ በመግባት ሦስተኛው ጎል ለሰበታ ያስቆጠረው መሐመድ አበራ በጉዳት በሜዳ ላይ 31 ደቂቃዎችን ካሳለፈ በኋላ ተቀይሮ ሊወጣ ተገዷል፡፡ ጨዋታውም በሰበታ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የሁለቱ ጎሎች ባለቤት የሆነው ናሚቢያዊው አጥቂ ጁኒያስ ናንጄቦ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።

ያጋሩ