ከፋሲል ከነማ ጋር ከተለያየ በኋላ ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረው ሙጂብ ቃሲም ወደ ሰሜን አፍሪካ ማቅናቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ሙጂብ ቃሲም ከፋሲል ከነማ ጋር ቀሪ ኮንትራት እያለው ውሉን አፍርሶ ወደ አልጄሪያው ክለብ ጄይኒስ ስፖርቲቭ ዲ ካቢሌ ለሦስት ዓመት ለመጫወት እንደተስማማ ተገልፆ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ሆኖም ግን የዝውውሩ አብዛኛው ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ ክለቡ በቀጥታ ለማስፈረም የነበረውን ስምምነት በመቀየሩ ምክንያት ዝውውሩ ሳይሳካ እንደቀረ ከዚህ ቀደም ዘግበን ነበር።
ይህን ተከትሎ አጥቂው ወደ ሀገር ውስጥ ክለቦች ፊቱን በማዞር ከፋሲል ከነማ ውጪ ከድሬደዋ ከተማ እና ሰበታ ከታማ ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቷል። ሆኖም ሁኔታው ተገቢ አይደለም በማለትም ተጫዋቹ ሪፖርት እንዲያቀርብ እና በባህር ዳር የቅድመ ውድድር ዝግጅት እየሰራ ያለውን ስብስብ እንዲቀላቀል ፋሲል ከነማ ትዕዛዝ አስተላልፎም ነበር።
ዛሬ ባገኘነው መረጃ መሠረት ደግሞ ትናንት ማምሻውን ሙጂብ ቃሲም ከአዲስ አበባ ኤርፖርት በመነሳት ወደ ቱኒዚያ በረራ ያደረገ ሲሆን ነገ አልያም ዛሬ ወደ አልጄሪያ የሚያቀና ይሆናል።
የጉዞውም ዋና ዓላማ የቀድሞው ፈላጊ ክለቡ ጄኤስ ካቢሌ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ እንደሆነ ሰምተናል። ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በቅርቡ እንደሚኖር ሲጠበቅ ዝውውሩ እንዲሳካ ናይጄሪያ የሚኖረው ኢትዮጵያዊው ወኪል ቢኒያም ሚዴቅሳ ትልቁን ድርሻ መውሰዱን አውቀናል።