ሶከር ሜዲካል- የሜዳ ላይ ቁስል ህክምና

እግር ኳስ ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን እና የጤና እክሎችን ከነመፍትሄዎቻቸው በምንዳስስበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን በዛሬው ዕለት የምንመለከተው በሜዳ ውስጥ የሚያጋጥሙ የቁስል እና የመድማት አደጋዎችን እና የሚታከሙበትን መንገድ ይሆናል፡፡

የመድማት እና የመቁሰል አደጋዎች በእግር ኳስ ተዘውትረው ከሚያጋጥሙ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለይም በታዳጊዎች እግር ኳስ ውስጥ ከሚያጋጥሙ ጉዳቶች በአራተኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ እነዚህ ጉዳቶች ሜዳ ላይ በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚከተሉት ነገሮች ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡

– የተጫዋቹ ከፍ ላለ ደም መፍሰስ ተጋላጭ መሆን እና አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም ከህመም እና ከሚወሰዱ መድኃኒቶች አንጻር ይመዘናል፡፡

– ሁሉም ተጫዋች የቴታነስ ክትባት መውሰዱን መታወቅ አለበት፡፡

– ማንኛውም አለርጂ ካለ መለየት መቻል አለበት፡፡

– በጨዋታ ወቅት ጉዳቱ ሲያጋጥም እንዴት እንደተከሰተ መታወቅ አለበት፡፡

– የደም መፍሰስን መቆጣጠር ፣ የቁስሉን ጥልቀት እና ስፋት መመልከት ያስፈልጋል

– ባዕድ እና ቁስሉን ሊበክሉ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ

– የነርቭ እና የደም ሥር ምርመራ ማካሄድ

– ቁስሉ ላይ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር መከላከል

ከቁስል እና መድማት አንጻር የፊፋ የጨዋታ ህግ ይህን ይመስላል

– ማንኛውም ደም እየፈሰሰው ያለ ተጫዋች ሜዳውን ለቆ መውጣት አለበት፡፡

– ዳኛው ደም ቆሟል ብሎ እስካላመነ ድረስ ተጫዋቹ ወደ ሜዳ አይመለስም፡፡

– ደም ያለበት ማልያ ማድረግ አይፈቀድም፡፡

ደም በሚፈስበት ወቅት እንደ ደም ሥሩ ዓይነት የተለያየ ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን ህክምናውም በዚሁ ምክንያት የተለያየ ይሆናል፡፡ ከአርተሪ (artery) የሚፈስ ደም እንደ ድንገተኛ ህመም መታየት ያለበት እና በአፋጣኝ ህክምና የሚያስፈልገው ነው፡፡ የውስጥ መድማትን ለማቆም በረዶ የሚጠቀሙ ሲሆን ወደ ውጪ የሚፈስ ደምን በተለያየ መንገድ ማቆም ሲቻል ከእነዚህም መካከል ጎዝ በመጠቀም ጫናን ማሳደር አንዱ ሲሆን እግርን ወደ ላይ በማንሳት ከቬን (vein) የሚፈስን ደም መቆጣጠር ሌላው መንገድ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደሁኔታው ሆኖ የጉዳቱን ቦታ መስፋት ያስፈልጋል፡፡

የቁስል ማከሚያ ቦርሳ ውስጥ የሚኖሩ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

– የሰመመን ወይም ማደንዘዣ መድሃኒት ( Lidocaine)

– የጸረ-ኢንፌክሽን መድሃኒቶች ( Chlorhexidine)

– ባዕድ ነገሮችን ከቁስል ለማስወገድ የሚጠቅሙ ማቴሪያሎች

– ቁስል የሚሰፋባቸው ማቴሪያሎች

– ቁስሉን ለማሸፈን የሚጠቅሙ ነገሮች

በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የመድማት አደጋ ከሚያጋጥሙበት የሰውነት ክፍል አንዱ ጭንቅላት ነው፡፡ ከጭንቅላት የሚፈሰው ደም ለመቆጣጠር ሊያስቸግር ይችላል ከዚህም የተነሳ በጥንቃቄ መታከም ያስፈልገዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ደሙን ለማቆም ጫናን ማሳደር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አጥንት ላይ ስብራት ተከስቶ ከሆነ መለየት ያስፈልጋል፡፡

ዓይን አካባቢ የመድማት አደጋ በሚደርስበት ወቅት ለበለጠ ምርመራ ወደ ዓይን ስፔሻሊስት መላክ ያስፈልጋል፡፡ ዓይን ውስጥ ተጨማሪ አደጋ አለመኖሩ እንደዚሁም ባዕድ ነገሮች አለመኖራቸው በምርመራ መታወቅ መቻል አለበት፡፡ የተጎዳው የዓይን ክፍል ላይ antibiotic ማድረግ እና መሸፈን ከዛም ወደ ድንገተኛ ክፍል መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ከመመለሳቸው በፊት ደም ሙሉ በሙሉ መቆሙ መታወቅ አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ቁስሉ ያለበት ቦታ ሙሉ በሙሉ መሸፈን እና መዘጋት አለበት፡፡ እንደ ጭንቅላት ዓይነት ተጓዳኝ ጉዳቶች አለመኖራቸውም መታወቅ አለበት፡፡