ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከነገ በስትያ ባህር ዳር ላይ ጨዋታ ያደርጋሉ

ባሳለፍነው ዓመት በተከናወነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከነገ በስትያ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

በ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፈው ከምድባቸው ማለፍ ያልቻሉት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጥቅምት 7 ለሚጀምረው የሊጉ ውድድር ወደ ስፍራው ከማምራታቸው በፊት ለበጎ አላማ የእርስ በእርስ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል። በአማራ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚከናወነው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ “በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው ጦርነት ለተጎዱ የአማራ ወገኖች” ገቢ ለማሰባሰቢያ እንደሚውል ተገልጿል።

እስከ ዛሬ አዲስ አበባ የነበሩት ፋሲል ከነማዎችም ረፋድ ላይ ለጨዋታው ባህር ዳር የገቡ ሲሆን ከሰዓት ከ9 ሰዓት ጀምሮም በባህር ዳር ስታዲየም ልምምዳቸውን ሰርተዋል። ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ከስብስቡ ጋር ከማይገኙት ተጫዋቾች ውጪ ግዙፉ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር እንደማይገኝ አውቀናል።

ከፌዴሬሽኑ የቀረበለትን ጥያቄ ዛሬ አመሻሽ ከ10 ሰዓት ጀምሮ የተመለከተው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቦርድም አውንታዊ ምላሽ እንደሰጠ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ይህንን ተከትሎም ነገ ከሰዓት ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ጉዞ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል። ጨዋታውም ከነገ በስትያ 10 ሰዓት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል። በጨዋታውም የኮቪድ-19 ህግጋትን በመከተል ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ያጋሩ