በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አቻ በተናቀቁት እና በመለያ የፍፁም ቅጣት ምት ሁለቱ የፍፃሜ ተፋላሚዎች በተለዩበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ እና መከላከያ በመጪው እሁድ በፍፃሜው የሚያገናኛቸውን ውጤት አስመዝግበዋል።
ጅማ አባጅፋር 1-1 ባህርዳር ከተማ (7-8 በመለያ ምት)
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የዕለቱ የመጀመሪያው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሁለት ሁለት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን የተመለከትንበት ነበር።
ባህርዳር ከተማዎች በሁለት አጋጣሚዎች አህመድ ረሺድ እና ፉአድ ፈረጃ ከመስመር ወደ ውስጥ ሰብረው ገብተው ያቀበሉትን ኳስ ተመስገን ደረሰ አስቆጥረው ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ በተመሳሳይ በጅማ አባጅፋሮች በኩል ደግሞ እዮብ አለማየሁ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ሸርፉ የሞከራት እና የግቡ ቋሚን ነክታ የወጣችበት እንዲሁም ከቅጣት ምት በአጭር ቅብብል የተጀመረውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ አስቆጠረ ሲባል የባህር ዳር ተከላካይ ደርሶ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በሒደት በመጠኑም ቢሆን እንደቀደሙት ደቂቃዎች የግብ እድሎችን መመልከት ባልቻንበት አጋማሽ በ38ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግቡን አስተናግዷል ፤ አህመድ ረሺድ ዱላ ሙላቱ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ዳዊት ፍቃዱ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሁለት የአጥቂ አማካዮቻቸውን ፍፁም ዓለሙ እና አብዱልከሪም ኒኪማን ቀይረው ያስገቡት ባህርዳር ከተማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተከታታይ ጥቃቶችን በአህመድ ረሺድ እና ተመስገን ደረሰ መሰንዘር ችለዋል።
ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች በ67ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። ፍፁም ዓለሙ ከመስመር አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አብዱልከሪም ኒኪማ ከግቡ ትይዩ የሞከረውን ኳስ ክሌመንት ሲያድንበት የተተፋውን ኳስ ዳግም ሲመለስ ተመስገን ደረሰ አግኝቶት አጥቂው በቀድሞ ቡድኑ ላይ ሊያስቆጥር ችሏል።
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ከደቂቃዎች በፊት ፉአድ ፈረጃን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ይበልጣል አየለ ባህርዳር ከተማን አሸናፊ ልታደርጎ የምትችል እጅግ አስደናቂ አጋጣሚን አግኝቶ የሞከራት ኳስ የግቡ አግዳሚ ሊመልስበት ችሏል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎችም ሁለቱ ቡድኖች ተጨማሪ ግቦችን ከማስቆጠር ይልቅ ጥንቃቄን መምረጣቸውን ተከትሎ ጨዋታው ተጨማሪ የግብ ሙከራዎችን ማስተናገድ ሳይችል ቀርቷል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱን ቡድኖች ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምቶች ባህርዳር ከተማ 8-7 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በመጨው እሁድ ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የጨዋታው ኮከብ በመሆን የተመረጠው የባህርዳር ከተማው ፉአድ ፈረጃ የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0 – 0 መከላከያ (4-5 በመለያ ምት)
ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያዎች አብዛኛውን የጨዋታ ደቂቃ ከኳስ ውጭ አራት በትይዮ የሚንቀሳቀሱ ተከላካዮች እንዲሁም ከእነሱ ለመከላከል ትኩረት የሰጡ አምስት አማካዮችን ተጠቅሞ እጅግ የተጠና የመከላከል እንቅስቃሴን ባሳዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን የመከላከያዎችን አቀራረብ ለመስበር በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ተጠቅሞ ለማጥቃት የነበረው ጥረት በተጫዋቾች የቦታ አጠቃቀም ክፍተት እምብዛም ውጤታማ ያልነበረበት አጋማሽ ነበር።
ነገርግን በአጋማሹ የተሻለ እድልን መፍጠር የቻሉት ጊዮርጊሶች ነበሩ በ8ኛው ደቂቃ ፀጋዬ መላኩ እና አላዛር በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል ያለፉትን ኳስ ፀጋዬ ሞከረ ለጥቂት ክሊመንት ያዳነበት እንዲሁም በ19ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በመከላከያዎች ተገጭቶ ሲመለስ ከሳጥን ውጭ የነበረው ሀይደር ኳሱን በቀጥታ ሞከረ ክሊመንት በድጋሚ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ ፤ በአጋማሹ ቢኒያም በላይ በግሉ ኳሶችን ከራሱ ሜዳ ይዞ ለመውጣት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ውጭ እምብዛም የተጠና የማጥቃት ጨዋታ ያልነበራቸው መከላከያዎች በ35ኛው ደቂቃ አኩቱ አማኑኤል ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ከላከው እና ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣበት ኳስ ውጭ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመድረስ ተቸግረው ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተጫዋቾች (በተለይ ያብስራ ተስፋዬ) በመከላከያ ሁለት የተጫዋቾች የመከላከል መስመር ውስጥ በተደጋጋሚ እንዲገኙ በማድረግ የተነጠለውን የአጥቂ ክፍል ከተቀረው የቡድኑ ክፍል ለማገናኘት ጥረት ቢያደርጉም የታሰበውን ያህል ውጤት ማስገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአጋማሹ ጊዮርጊሶች በ88ኛው ደቂቃ ሻይዱ ሙስጠፋ ከግራ መስመር አሻግሮ ፀጋዬ መላኩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣበት ኳስ ውጭ እድሎችን መፍጠር ሲቸገሩ በአንፃሩ መከላከያዎች በ58ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ በግሩም ሁኔታ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈተትን ኳስ አኩቱ አማኑኤል ከባህሩ ነጋሽ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት እንዲሁም በ80ኛው ደቂቃ ገናናው ከራሱ ሜዳ ለቡድን አጋሮቹ ያሻገረውን ኳስ ባህሩ ነጋሽ ግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ያመለጠችውን ኳስ ዳግም ደርሶ ለጥቂት ያወጣባቸው ኳሶች የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ።
መደበኛው ዘጠና ደቂቃ 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በፍፃሜው ባህርዳር ከተማን የሚገጥመውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት መከላከያ 5-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለእሁዱ ፍፃሜ መድረሱን አረጋግጧል።
በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሀል ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ የጨዋታው ኮከብ ሲሰኝ የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።