የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሩዋንዳን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል

ከሜዳው ውጪ ሩዋንዳን አራት ለምንም አሸንፎ ዛሬ ከሰዓት የመልሱን ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በድምሩ 8-0 አሸንፎ ወደ ሦስተኛው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ማለፉን አረጋግጧል።

አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከሳምንት በፊት ወደ ኪጋሊ አምርተው የሩዋንዳ አቻቸውን 4-0 ካሸነፈው የመጀመሪያ አሰላለፋቸው በሀዘን ምክንያት ከስብስቡ ውጪ የሆነችውን ብዙዓየሁ ታደሠን ብቻ በነፃነት ፀጋዬ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም የሚሞክሩትን ሩዋንዳዎች በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ በልጠው ታይተዋል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ናርዶስ ጌትነት ከርቀት ያሻገረችው ኳስ ማንንም ሳይነካ ነጥሮ መረብ ላይ አርፎ መሪ ሊያደርጋቸው ቢቃረብም ኳሱ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ ወትቷል።

ሩዋንዳዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ዛዋዲ ዩሳናሲ ከቅጣት ምት ወደ ኢትዮጵያ ግብ ከመታችው ሙከራ ውጪ አንድም የጠራ ዕድል እስከ 22ኛው ደቂቃ ድረስ አላደረጉም። በዚህ ደቂቃ ግን የቡድኑን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገችው ዛዋዲ ዩሳናሲ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ብቻዋን ረጅም ሜዳ በመጓዝ ጥሩ ሙከራ አድርጋ ነበር። ይህቺው ተጫዋች ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ ለማስቆጠር ጥራ ነበር።

እስከ ግማሽ ሰዓት ድረስ ግብ ጋር ሲደርሱ መቻኮል ውስጥ ሲገቡ የነበሩት የአሠልጣኝ ፍሬው ተጫዋቾች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግን ፍሬያማ ሲሆኑ ታይቷል። በ32ኛው ደቂቃ ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ለመጠቀም የጣሩት ተጫዋቾቹም ኳሱን በግንባር ከመረብ ጋር ከመቀላቀል ቢጥሩም ተከላካዩዋ ራቲፋ ኡሙትሲዋሲ ከመስመር ላይ አውጥታዋለች። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን በጥሩ መናበብ ወደ ሩዋንዳ የግብ ክልል ያመራው ቡድኑ በመሳይ ተመስገን አማካኝነት ግብ አስቆጥሮ ወደ መሪነት ተሸጋግሯል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ አረጋሽ ወደ ግብ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ኤልዛቤት ሙቲይማና ስትተፋው ያገኘችው ቱሪስት ለማ እንደ ምንም ታግላ ኳሱን ጎል አድርጋዋለች።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሲያደርጉ የነበሩትን ጫና በሁለተኛው አጋማሽ አጠናክረው የቀጠሉት ኢትዮጵያዎች በ57ኛው ደቂቃ በአረጋሽ ካልሳ አማካኝነት ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ63 እና 64ኛው ደቂቃ በመሳይ ተመስገን እና ረድኤት አስረሳከኝ አማካኝነት ሌሎች ጥቃቶችን ሰንዝረው ነበር። በ67ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሦስተኛው ግብ ባለቤት አረጋሽ ካልዳ በግራ መስመር እየገፋች የሄደችውን ኳስ ወደ ግብ ብትመታውም የግቡ ቋሚ መልሶባታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የቆሙ እና ረጃጅም ኳሶችን ብቻ ግብ ለማስቆጠሪያነት ሲጠቀሙ የነበሩት ሩዋንዳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይህንን አጨዋወትም ሆነ ሌላ ሥልት በመቀየስ ከባዱን ፈተና ለማለፍ አልሞከሩም። በአንፃሩ ቀለል አድርገው መጫወት የቀጠሉት ኢትዮጵያዎች በ69ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ ከርቀት በመታችው የቅጣት ምት አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ይህ ግብ ከተቆጠረ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ሩዋንዳዎች ከቅጣት ምት ሰንዝረው መክኖባቸዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ግን በዛዋዲ ዩሳናሲ እና ሊዲያ ኡዛይሴንዛ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። ይህ ቢሆንም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የጽሕፈት ቤት ሀላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ሰውነት ቢሻው እና የቴክኒክ ሀላፊው አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ወደ ሜዳ ወርደው ተጫዋቾቹን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም አዲስ አበባ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከተረላቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሦስተኛ ዙር የማጣሪያ መርሐ-ግብር ከቦትስዋና እና አንጎላ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል። የቦትስዋና ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ አንጎላን 4-1 አሸንፎ የመልሱን ጨዋታ እየተጠባበቀ መሆኑ ልብ ይሏል።

ያጋሩ