ዲኤስቲቪ ለኢትዮጵያዊያን የቀጥታ ስርጭት ባለሙያዎች ያዘጋጀው ሥልጠና ተጀመረ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን በኢትዮጵያዊያን የቀጥታ ስርጭት ባለሙያዎች ለማዋቀር ያለመ ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ከጥቅምት 7 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ በአስራ ስድስት ክለቦች መካከል ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተጠናቀቀው የ2013 የውድድር ዘመን ጀምሮ የቀጥታ ሽፋን በሱፐር ስፖርት ያገኘው ይህ ውድድር ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ አየር ላይ ይውላል፡፡ በአርባ አንድ ሀገራት ውስጥ ቅርንጫፎች ያሉት መልቲ ቾይዝ ይህን የፕሪምየር ሊግ ውድድር የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በሀገር ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች እንዲሰራ በማሰብ ከሳምንታት በፊት ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት በርካቶች ተመዝግበው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም በድምሩ ሀያ ስድስት ሙያተኞች ተመርጠው በዛሬው ዕለት ሥልጠና መውሰድ ጀምረዋል፡፡

የቴክኒክ ፣ የካሜራ እና የፕሮዳክሽን ባለሙያዎችን በጥምረት አቅፎ ይህ የተግባር ፣ የንድፈ ሀሳብ እና የክፍል ሥልጠና በዛሬው ዕለት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል መሰጠት የጀመረ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሀያ ቀናትም እንደሚቆይ የመልቲ ቾይዝ ህዝብ ግንኙነት አቶ ደመቀ ከበደ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ሥልጠናው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን በማብቃት ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ መጥተው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ባለፈው ዓመት በላይቭ ፕሮዳክሽን የሰሩ የውጪ ሀገር ባለሙያዎችን ቢያንስ ወደ 30 በመቶ የመቀነስ ሀሳብ አለው። በሥልጠናው ተካፋይ የሆኑ ሙያተኞችን አብቅቶ ወደ 70 በመቶ በማሳደግ የቀጥታ ስርጭቱ በሀገራችን ሙያተኞች እንዲሰራም ታስቧል። ለሀያ ቀናት የሚሰጠውን ሥልጠና በዋነኛነት የዲኤስቲቪ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና በኬንያ የሚገኘው የዲኤስቲቪ ላይቭ አይ ፕሮዳክሽን ቲም ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን በሥልጠናው ተካፋይ የሆኑ ባለሙያዎች በዋናነት ዓለምአቀፍ ልምድ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተግባር ሥልጠናውን በዋናነት በትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከቀናት በኋላ ሲጀመር በሀዋሳ ተገኝተው የኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ልምድ የሚቀስሙበት ዕድል እንደተመቻቸም ተገልፆልናል፡፡