የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ከመዲናው ውጪ ሊካሄድ ይሆን?

በባህር ዳር ከተማ እና መከላከያ መካከል የሚደረገው የ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፄሜ ጨዋታ ከአዲስ አበባ ውጪ ሊደረግ እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ተገንዝባለች።

በአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው የመዲናው የዋንጫ ውድድር ዘንድሮም በስምንት ክለቦች መካከል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በውድድሩ ምድብ አንድ እና ሁለት ተደልድለው የነበሩት መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማም በግማሽ ፍፃሜው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋርን በመርታት ለፍፃሜው ፍልሚያ ማለፋቸው ይታወቃል።

ቀድሞ በወጣው መርሐ-ግብር ውድድሩ ሙሉ ለሙሉ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ ቢታወቅም በአማራ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ የፍፃሜው ጨዋታ ወደ ባህር ዳር ሊዘዋወር ነው። የአማራ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጨዋታው ገቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲሆን ያቀረበውን ጥያቄ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እያጤኑት ሲሆን ሁለቱ የፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦች ግን ሀገራዊውን ጥሪ ተከትሎ የቀረበውን ጥያቄ እንደተቀበሉት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ከሰዓታት በኋላ በሚያደርገው የሥራ-አስፈፃሚ ስብሰባ የፍፃሜው እና የደረጃው ጨዋታ ወደ ባህር ዳር የመዞሩን ጥያቄ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ሰምተናል።

ያጋሩ