ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከከፍተኛ ሊጉ ውድድር ሊጀምር ነው

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ተካፋይ የሆነው ክለብ በድጋሚ ሊቋቋም እንቅስቃሴ ላይ ወዳለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጠቃለል ነው፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለቦች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ክለብ ነበር። በ1976 የተመሰረተው ክለቡ በ2004 ኢትዮጵያ ባንኮች የሚለውን ስያሜ በመቀየር እስከ 2009 በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚል መጠሪያ ሲወዳደር ከቆየ በኋላ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ለመውረድ በመገደዱ በወቅቱ የነበሩ የክለቡ የበላይ አካላት በሰጡት መግለጫ ክለቡ የወንድ ቡድኑን እንዳፈረሰ እና በሴት ቡድኑ ብቻ እንደሚቀጥል መገለፁ ይታወሳል፡፡

ከዋናው ቡድን ባለፈ የታዳጊ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች ባለቤት የነበረው እና በርካታ ተጫዋቾችን ለሀገራችን እግር ኳስ ማብቃት የቻለው ይህ አንጋፋ ክለብ ለአራት ዓመታት ከውድድር ከራቀ በኋላ ዘንድሮ በድጋሚ ሊመሰረት እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይ አካላት በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቡድኑ ተወዳድሮ ከሚመጣ ይልቅ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ያለን ክለብ በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዚህ ቀደም ወደነበረበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በፍጥነት ለመመለስ በማሰብ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን /ኢኮሥኮ/ ለመጠቅለል የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በ1990ዎቹ መጨረሻ ተመስርቶ እስከ 2010 ድረስ የኢትዮጵያ ውሀ ሥራዎች በሚለው መጠርያው ሲወደደር ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮሥኮ) የተጠቃለለው ክለቡ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ እየተሳተፈ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሽጦ ሊዛወር መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ሰለሞንን ጠይቀን እንደገለፁልን ከሆነም በቅርቡ በሚኖር ጋዜጣዊ መግለጫ በዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጥ ይሆናል።