ዛሬ ከሰዓት በኢሊሊ ሆቴል እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ከኤልኔት ግሩፕ ድርጅቶች ጋር የገንዘብ እና የዓይነት ስፖንሰርሺፕ ተፈራርሟል።
ከዚህ ቀደም ከዋሊያ ቢራ እና ውዳሴ ዲያጎኖስቲክ ጋር የሥራ ግንኙነት የፈጠረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ የወንዶች ብሔራዊ ቡድኑን የተመለከተ ተጨማሪ አጋር አግኝቷል። ከፌዴሬሽኑ ጋር የተፈራረመው ተቋም ኤልኔት ግሩፕ የሚሰኝ ሲሆን በውስጡ ዘጠኝ ድርጅቶችን አቅፏል። ከእነዚህ ውስጥ ታክሲዬ በመባል የሚታወቁትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መኪኖች የሚገጣጥመው በኢንጂነሪንግ እና ሪልስቴት ሥራዎች ላይ የተሰማራው ኤልኔት አውቶ ኢንጂነሪንግ፣ ኤልኔት ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሥራ አጦች ፣ የአዕምሮ ህሙማን እና በመንገድ ዳር በተጣሉ የጋማ ከብቶች ህክምና ላይ የሚሰራው ኤል ኔት ፋውንዴሽን ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ተቋም ጋር ያደረገው ስምምነት ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚዘልቅ ይሆናል። ስምምነቱ በገንዘብ እና በዓይነት የተከፋፈለ ሲሆን በዋነኝነት ኤልኔት ግሩፕ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የተከፋፈለ በዓመት ስባት ሚሊየን ብር በድምሩ የ28 ሚሊየን ብር የስፖንሰርሺፕ ክፍያ ይፈፅማል። ከዚህ ውጪ በድርጅቱ የሚገጣጠሙ እና 1.8 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ሁለት መኪናዎች በየዓመቱ ለፌዴሬሽኑ የሚያበረክት ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ በማንኛውም ውድድር አሸናፊ በሚሆንባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ማበረታቻ የሚሆን አምስት መቶ ሺህ ብር ይሰጣል። በሌላኛው የስምምነቱ ክፍል ደግሞ በየዓመቱ የብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴ ውስጥ የተሻለ አቅም ያሳየ ተጫዋች ወይም አሰልጣኝ በህዝብ ተምርጦ በየዓመቱ የአንድ መኪና ስጦታ የሚበረከትለት ይሆናል።
በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ በኩል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የልምምድ ማልያ ላይ ኤልኔት ግሩፕን ማስተዋወቅ የሚጠበቅ ሲሆን ብሔራዊ በድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከ 6-10 በሚደርሱ ባነሮች እንዲሁም በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ድርጅቱን የማስተዋወቅ ሥራ ይጠበቃል።
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የዛሬውን ጨምሮ በቀጣይ ከአንድ ባንክ ጋር ይፋ የሚደረግ ሌላ የስፖንሰርሺፕ ሥምምነት በመፈፀም ገቢውን ከ 15 ዓመት በታች የታዳጊዎች ፕሮጀክት እና ሌሎች መሰርተ ልማቶች ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል። የኤልነት ግሩፕ ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ናኦል ቢራቱ በበኩላቸው ተቋማቸው ስለሚሰራቸው ሥራዎች እና በውስጡ ስላሉ ድርጅቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ስምምነቱ ድርጅታቸውን በማስተዋወቁ ረገድ ያየውን ሚናም አንስተዋል።