በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ለገቢ ማሰባሰቢያነት እንዲውል በፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የተደረገው ጨዋታ በዐፄዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአማራ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የተዘጋጀውን ጨዋታ ለመመልከት የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ድረስ ፣ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አማኑኤል ፈረደ፣ የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ጣሂር እንዲሁም ሌሎች የክልሉ የመንግስት ባለስልጣናት እና የኢትዮጵያ ብሔራዎ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተገኝተዋል።
መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ለዐይን ሳቢ ሳይሆን መደረጉን ቀጥሏል። በ13ኛው ደቂቃም ሳሙኤል ዮሐንስ ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ መትቶት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርጎ ነበር። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሮቤል ተክለሚካኤል አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥቃት ሰንዝረው የግብ ዘቡ ሚኬል ሳማኪ አድኖባቸዋል።
የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማስመልከት ያልቻለው ጨዋታው በ35ኛው ደቂቃ በአንፃራዊነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃም ፍቃዱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት የዐፄዎቹ አምበል አምሳሉ ተጠቅሞት ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ፍቃዱ ዓለሙ ከሰዒድ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ሊቀይረው ጥሮ መክኖበታል።
እጅግ ፉክክሩ ተሻሽሎ የቀረበው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ የሰሉ ሙከራዎችን ማስተናገድ ይዟል። በ53ኛው ደቂቃም ቡናዎች በገዛኸኝ ደሳለኝ አማካኝነት የመጀመሪያ የአጋማሹን ሙከራ ሲያደርጉ ፋሲሎች ደግሞ ከደቂቃ በኋላ በሳሙኤል አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርገዋል።
በ60ኛው ደቂቃ በጉዳት ተከላካያቸውን ከሜዳ አስወጥተው (ለህክምና) የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ቡናዎች ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አግኝቶት መረብ ላይ በጥሩ አጨራረስ አሳርፎታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው በረከት ደስታ ከግራ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ መሐል እየገፋ በመሄድ ወደ ግብ የመታው ኳስ ተከላካይ ጨርፎ ጎል ሆኗል።
በደቂቃዎች ልዩነት ግቦችን ያስተናገዱት ቡናማዎቹ በያብቃል ፈረጃ እና እንዳለ ደባልቄ አማካኝነት ተከታታይ ሙከራዎችን አድርገው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ ቡድኖች አላማውን ደግፈው በመምጣታችች ከክብር እንግዶቹ የምስክር ሰርተፍኬት የተቀበሉ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ የተባለው በረከት ደስታም የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከአሠልጣኝ ውበቱ ተረክቧል። ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ የሆነበትን ፋሲል ከነማ ደግሞ ያሸነፈበትን ዋንጫ በአምበሎቻቸው አማካኝነት ተቀብለዋል።