የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ከደቂቃዎች በፊት ባህር ዳር ገብተዋል

በነገው ዕለት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ ጨዋታ የሚያደርገው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ባህር ዳር ገብቷል።

በዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ማጣሪያ በምድብ ሰባት የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ነገ እና ማክሰኞ ተከታታይ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቀናቶች በፊት ጨዋታው ወደሚደረግበት ከተማ (ባህር ዳር) በመምጣት ልምምዱን ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ ደቡብ አፍሪካዎች ባህር ዳር ደርሰዋል።

በቻርተር አውሮፕላን ትናንት ምሽት ከሀገራቸው የተነሱት ደቡብ አፍሪካዎች ለሊት አዲስ አበባ ቦሌ ዐየር ማረፊያ ደርሰው ነበር። ልዑኩም የመጣበትን የግል አውሮፕላን ቦሌ አሳርፎ ማለዳ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ወደ ባህር ዳር ጉዞ አድርጓል። 39 የልዑካን ቡድን የያዘው ስብስቡም በኩሪፍቱ ሪዞርት ማረፊያውን ያደረገ ሲሆን ከጨዋታው በፊት 10 ሰዓት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምዱን የሚሰራ ይሆናል።