በነገው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለመግጠም እየተዘጋጁ ያሉት ደቡብ አፍሪካዎች በአሠልጣኛቸው እና አምበላቸው አማካኝነት መግለጫ ሰጥተዋል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ነገ 10 ሰዓት የሚገጥመው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኙ ሁጎ ብሩስ እና አምበሉ ቴቦሆ ሞክዌና አማካኝነት ከአመሻሽ 11:30 ጀምሮ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኝ ሁጎ ብሩስ ጎዞዋቸውን በተመለከተ ተከታዩን አወዛጋቢ ሀሳብ ሰጥተው ገለፃቸውን አድርገዋል።
“ነገ ወሳኝ ጨዋታ ነው የምናደርገው። ግን በዚህ የመጫወቻ ሜዳ ወሳኙን ጨዋታ ማድረግ ከባድ ነው። የመጫወቻ ሜዳው ለመጫወት አይመችም። ከዚህ በላይ ጥሩ ሜዳ ያስፈልግ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ጨዋታውን የምናደርግበት ከተማ ቪዛ እና ፓስፖርት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስላልሆነ አዲስ አበባ ትራንዚት ለማድረግ ተገደናል። ይህ የኢትዮጵያን ስልት ሊሆን ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል። ጨዋታውንም ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል።
“የነገ ተጋጣሚያችን ጠንካራ ቡድን ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ቡድን ነው። ይህንን ተከትሎ ጠንክረን ወደ ሜዳ በመግባት ጥሩ መጫወት አለብን። እንደምናሸንፍም አስባለሁ።” ብለዋል።
የነገውን ጨዋታ ቢያሸንፉ እንኳን ምድቡ ከባድ እንደሆነ የጠቆሙት አሠልጣኙ ከሁለቱ ቡድኖች ጋር በተያያዘ ያለውን ታሪክ ተከትሎ የቀረበላቸውን ጥያቄ “ታሪክ ታሪክ ነው። ያለፈ ታሪክ ያለፈ ነው። ነገ አዲስ ጨዋታ ነው። ትኩረታችንን በታሪክ በተመዘገበው ውጤት ላይ አናደርግም።” በማለት መልሰዋል።
በተከታይነት ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጠየቁት አሠልጣኙ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው። ከዛምቢያ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ አይቻለሁ። በጣም ጥሩ አጨዋወት ነው ያላቸው። አደገኛ ተጫዋቾችም አሏቸው። ይህንን አውቀን ነው ነገ ወደ ሜዳ የምንገባው።”
በንግግራቸው መካከል ቡድኑን ለጨዋታው ለማዘጋጀት ሰፊ ጊዜ እንዳላገኙ ነገርግን ይህ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ችግር እንደሆነ አስረድተው ባለው ጊዜ ልምምድ ላይ ባዩት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን አመላክተው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው የቡድኑ አምበል ቴቦሆ ሞክዌናም ስለ ጨዋታው ያለውን ሀሳብ አጋርቷል። “ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል። የነገውም ጨዋታ ቀላል እንደማይሆን እንረዳለን። ጨዋታውንም ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን። ባህር ዳርም የተገኘነው ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው።”