ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል

👉”የሊግ አክሲዮን ማህበሩ መሰል ስልጠናዎችን የማዘጋጀት ስልጣን የለውም” – መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

👉”የእግርኳሳችን ደረጃ ለማሻሻል ጠንክረን እንሰራለን” – ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ላይ ትምህርት ሲሰጥ የቆየው የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ሊግ ካምፓኒው ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይህ ስልጠና በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ሲጠናቀቅ በፕሮግራሙ ላይ የሊግ ካምፓኒው ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና ከመልቲ ቾይዝ በኩል ወ/ሮ ሰሎሜ ናይዶ በክብር እንግድነት ታድመዋል።

በዕለቱ የስልጠናውን ማብቂያ አስመልክቶ የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል።

“በመሰረታዊነት ይህ ስልጠና የዛሬ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ነበር። ነገርግን የጉዞ ክልከላዎችን ተከትሎ ወደ ዘንድሮ ሊገፋ ችሏል። እንደምታውቁት አክሲዮን ማኅበሩ መሰል ስልጠናዎችን የማዘጋጀት ስልጣን የለውም። ነገርግን የሀገራችን የእግርኳስ አሰልጣኞች የሚገኙበትን ደረጃ በደንብ የተረዳው ማህበሩ ከስልጣኑ ውጭ ይህን ስልጠና ለማዘጋጀት ተገዷል። ወደፊትም ክለቦች ስልጠናን በተመለከተ መጠቀም የሚችሉበት ጥግ እስኪደርሱ እንቀጥላለን። በሒደት ከሦስት እና አራት ዓመታት በኃላ ዛሬ ስልጠናውን ከወሰዳችሁት ውስጥ የተወሰናችሁት በሌላ ሀገራት ሄዳችሁ ለማሰልጠን እንደምትበቁ ተስፋ አደርጋለሁ። ከስልጠናው ብዙ ነገር እንዳገኛችሁ እና ይህንን ደግሞ በሜዳ ላይ እንደምንመለከት ተስፋ አደርጋለሁ።

“በዚህ ስልጠና ያገኛችሁትን እወቀት ወደ ክለቦቻችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ እድሜ እርከን ቡድኖች ውስጥ አስርፃችሁ የተሻለ ነገር ትፈጥራላችሁ የሚል እምነት አለኝ። ስልጠናው በዚህ አያበቃም፤ ምክትሎቻችሁ እና የወጣት ቡድኖች አሰልጣኞችም የዚሁ አካል ይሆናሉ። አዲስ የምንጀምረው የውድድር ዘመንን ከአምናው በተሻለ ከፍታ እንጀምራለን የሚል አቋም አለን።

“እንደምታውቁት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ከብሔራዊ እግርኳስ ፕላን ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። አውሮፓውያኑ ሀገራት በምን ፎርሜሽን እና የጨዋታ መንገድ እንደሚጫወቱ ጥርት ባለ መንገድ ይታወቃል፤ በተወሰነ መንገድ ይለያዩ እንጂ አብዛኞቹ የአውሮፖ ሀገራት አንድ የጋራ ወደሆነ የጨዋታ መንገድ እየደረሱ ይገኛል። በእኛ ሀገር አውድ ግን በጋራ መክረን የተስማማንባቸው ስልጠናዎች እና በጥቅሉ የእግርኳስ ፖሊሲዎች የሉንም።

“ሁለተኛው ትልቁ ችግር በሀገራችን ያለው ችግር 30 (40) ተጫዋቾችን ለጥቂት ወራት በማሰልጠን ለአፍሪካ ዋንጫ እና ሌሎች ውድድሮች ማለፍ የሚቻል ይመስለናል። ይህ አካሄድ ከዚህ ቀደምም ነበር፤ አሁንም አለ። ነገርግን እኔ የማምነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጠንካራ ክለቦችን ለመፍጠር ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። በዚህ ሂደትም ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር ይቻላል ብዬ አምናለሁ። አክሲዮን ማህበሩ ገና ከጅምሩ ከፌደሬሽኑ ጋር ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ የሚለቀቁት ለዘጠኝ ቀናት ብቻ በመሆኑ ዙርያ ተስማምተን የቀደመውን ለ30 (40) ቀናት ዝግጅት ሦስት ተጫዋቾች እና ከዛ በላይ ያስመረጡ ክለቦች ከውድድር የሚያርፉበትን አካሄድ አስቀርተናል። ሌላው ውድድሮች የሚጀመሩት አስቀድሞ በተቀመጠና እንደ ህግ በሁሉም በሚከበር ቀን እንዲሆን አድርገናል።”

በማስከተል ከስልጠናው ያገኙትን ጠቀሜታ አሰልጣኞቹን በመወከል ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ተከታዩን ሀሳብ ተናግረዋል።

“በሊጉ በመሥራት ላይ በሚገኙ አሰልጣኞች ስም የሆላንድ እግርኳስ ማኅበር፣ ዲኤስቲቪ እና የሊግ አክሲዮን ማኅበሩን ይህን የማነቃቂያ ስልጠና ስላዘጋጁ ለማመስገን እወዳለሁ። ለአምስት ቀናት የቆየው ስልጠና አሰልጣኞች አዳዲስ ዕይታዎችን ያገኙበት እና አቅማችን ለማሳደግ የሚያግዝ ነበር። በስልጠናው በአሰልጣኞች መካከል ከልምዶችን ከመለዋወጥ ባለፈ ለወደፊት የስልጠና ጉዟችን የሚያግዙ ጠቃሚ እውቀቶችን ያገኘንበት ነበር።”

“መሰል ስልጠናዎች ቢያንስ በዓመት ለሁለት ጊዜያት ካልተቻለም ለአንድ ጊዜ መካሄድ ይኖርባቸዋል። ሌላው ስልጠናዎች የሚሰጡበት ወቅት በትኩረት ሊታይ ይገባዋል። ምናልባት ይህ ስልጠና ውድድሮች በማይኖርባቸው በእረፍት ወቅቶች ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ትኩረት አድርገን መካፈል እንችል ነበር። በመጨረሻም በስልጠናው የተካፈልን ሁሉም አሰልጣኞች በቀጣይ ጠንክረን በመሥራት እና በተለያዩ ጊዜያት እየተገናኘን ውይይቶችን በማድረግ የእግርኳሳችን ደረጃ ለማሻሻል ጠንክረን እንሰራለን።” ብለዋል።


በመጨረሻም ስልጠናውን ለወሰዱት አሰልጣኞች የዕውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ለስልጠናው መሳካት እና ለአምስት ቀናት የቆየውን ስልጠና በመስጠት ትልቁን ሚና ለተወጡት ሦስት አሰልጣኞች ሮጀር ሾውናር (ከሆላንድ)፥ ፍራንሲስ ይላውዚ (ከኬንያ) እና ሬይሞሆ ናሮታ (ደቡብ አፍሪካ) የኢትዮጵያ ባህልን የሚገልፁ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል።