👉”ተጫዋቾቻችን በጥሩ መነሳሳት እና ጤንነት ላይ ይገኛሉ” ውበቱ አባተ
👉”ታፈሰ ሰለሞን ጥሪ በተደረገለት ወቅት መገኘት አልቻለም ፤ ዘግይቶ በምሽት….” ውበቱ አባተ
👉”ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል” ጌታነህ ከበደ
👉”በአንድም በሌላም መንገድ ነገ በማንደግመው መልኩ ውጤቱን ልናገኝ እንችላለን። ነገርግን እሱ ለእኛ ብዙ ጠቃሚ አይደለም” ውበቱ አባተ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ያደርጋል። ከጨዋታው በፊት የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሁጎ ብሩስ እና አምበሉ ቴቦሆ ሞክዌና የሰጡትን መግለጫ ከደቂቃዎች በፊት ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ በኩሪፍቱ ሪዞርት የሰጡትን ገለፃ ይዘን ቀርበናል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ለጨዋታው የተዘጋጁበትን መንገድ አስረድተዋል።
“ከደቡብ አፍሪካ ጋር ላለብን የደርሶ መልስ ጨዋታ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገን ከመስከረም 14 ጀምሮ ልምምድ ስናደርግ ቆይተናል ፤ በዝግጅት ወቅተ አቅደን ከነበረው አንፃር የወዳጅነት ጨዋታ ካለማድረጋችን ውጭ ጥሩ የሚባል የልምምድ ጊዜ አሳልፈናል። ተጫዋቾቻችን በጥሩ መነሳሳት እና ጤንነት ላይ ይገኛሉ።” ካሉ በኋላ በቅድሚያ ተጫዋቾችን ጠርተው በጊዜው ስላላገኙበት እና ታፈሰ ሠለሞንን ከስብስቡ ውጪ ስላደረጉበት ምክንያት ይህንን ብለዋል።
“ጥሪ አልደረሰንም በማለት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩ። ነገርግን ፌደሬሽኑ እና ከክለቡ ጋር በመነጋገር ዝግጅቱን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ችለናል። ታፈሰ ሰለሞን ጥሪ በተደረገለት ወቅት መገኘት አልቻለም። ዘግይቶ በምሽት እንደገባ ነው መረጃ የደረሰኝ እና በማግስቱ በነበረን ልምምድ ላይም መገኘት አልቻለም። በዚህም ሁኔታ ከእኛ ጋር መቀጠል ስማይችል በዲሲፕሊን ከቡድኑ እንዲቀነስ አድርገናል። በምትኩም በዛብህን ቀላቅለን እስካሁን በልምምድ ላይ እያሳለፈ ይገኛል።” ብለዋል።
በተከታይነት በዚምባቡዌው ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር ስለመቸገራቸው እና ይህን ነገር ለአሁኑ ጨዋታ ተቀርፋል ወይ ተብለው የተጠየቁት አሠልጣኙ “እርግጥ ቡድን በአንድ ጀምበር አይገነባም ፤ የጨዋታው የማስጀመርያ ፊሽካ ተነፍቶ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ በየትኛውም ሰአት ግብ ሊቆጠር ይችላል ከዚያ በላይ ግብ ለማስቆጠር የምንሄድባቸውን መንገዶች ለማረም እየሞከርን ነው። ወደ ውድድሩ ስንገባ ከምድቡ ማለፍን ታሳቢ አድርገን እንደመጀመራችን ጥሩ ነገር ነው ያለው። ከግብ ማግባት ጋር ተያይዞም ብዙ መጥፎ ነው ብሎ የሚያስፈርጅ ነገር የለም። ምናልባት በሁለት ጨዋታ አንድ ግብ ማስቆጠራችን ችግር ያለ ሊያስመስል ይችላል። ነገር ግን የተጋጣሚያችን ደረጃ ከግምት ስናስብ ለዛ ሩቅ እንዳልሆንን ይሰማኛል። በተደጋጋሚ ወደ ጎል የምንደርስበትን መንገድ ማሻሻል ላይ በደንብ መስራት ይኖርብናል። መንገዱ ከተስተካከለ ግቦቹ በየትኛውም ደቂቃ መገኘት ይችላሉ። ለዛም የሚሆኑ ስራዎች እየሰራን እንገኛለን።”
በመጨረሻ በሁለቱ ጨዋታዎች ማሳካት ስላቀዱት ነገር ተጠይቀው ሀሳብ መስጠት የቀጠሉ ሲሆን በዋናነት የተጠና አጨዋወት መከተልን ምርጫቸው እንዳደረጉ አመላክተዋል።
“ሁለቱ ጨዋታዎች በተከታታይ የሚደረጉ እንደመሆናቸው ጥያቄው መነሳቱ መጥፎ አይደለም ፤ ግን በየጨዋታው የምንከተለው መንገድ ውጤቱን የትኛውም ነገር ቢሆን የምንሄድበትን መንገድ ማረሙ መንገዳችን ይወስነዋል። በአንድም በሌላም መንገድ ነገ በማንደግመው መልኩ ውጤቱን ልናገኝ እንችላለን። ነገርግን እሱ ለእኛ ብዙ ጠቃሚ አይደለም። ከውጤቱ በላይ መንገዳችን ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው ሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ጥሩ የምንቀሳቀስ ከሆነ ማሸነፍ ከዛ ቀጥሎ የሚመጣ ነገር ነው።”
ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ በኋላ ደግሞ የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ተጫዋቾቹን ወክሎ ስለ ዝግጅታቸው አጭር ሀሳብ ሰጥቷል።
“ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል ፤ ምንም አይነት ጉዳት የለብንም ሙሉ ስብስቡ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል ከገባንበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል።”