የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዕሁድ ይጠናቀቃል

በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት ሲደረግ የከረመው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የፊታችን ዕሁድ በደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርአት ፍፃሜውን ያገኛል፡፡

ከተመሰረተ አንድ ዓመት ለማስቆጠር ጥቂት ጊዜን በሚጠብቀው የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት ከመስከረም 15 ጀምሮ በአምስት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል በዙር ሲደረግ የሰነበው የመጀመሪያው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የፊታችን ዕሁድ መስከረም በደማቅ የመዝጊያ ሥነ ስርአት ፍፃሜውን በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ያደርጋል፡፡ እንደ ጅምር ጠንካራ ጎኖች የታዩበት እና ክለቦች ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አስቀድመው ራሳቸውን የሚገመግሙበት ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ክለቦች መካከል ሲደረግ የነበረ ሲሆን የፊታችን እሁድም በይፋ ይጠናቀቃል፡፡

ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕናን ባቀፈው የዙር መርሀግብር እያንዳንዱ ክለቦች አራት አራት ጨዋታዎችን ያከናወኑ ሲሆን የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ክለብ የሆነው ሰበታ ከተማ ዕሁድ የመጨረሻ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው ቀደም ብሎ በሰበሰበው ዘጠኝ ነጥብ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን አውቆ ሀዋሳ ከተማን 9፡00 ሲል ይገጥማል። ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት 7፡00 ሲል ሀድያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን በደረጃ ለማጠናቀቅ የሚረዳቸውን መርሀግብር ይከውናሉ፡፡

በዕለቱም ልዩ የመዝጊያ ሥነ ስርአት እንደሚኖር የውድድሩ የሚዲያ አጋር የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበን ጠይቃ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ የነገሩን ሲሆን አሸናፊ ለሆነው ክለብ የዋንጫ እንዲሁም በውድድሩ ለደመቁ ኮከቦች በጎፈሬ እና በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ የተዘጋጀ ሽልማት እንደሚኖር ጠቁመውናል። በውድድሩ ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ሽልማትም የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት በተሻለ የጥራት ደረጃ ሊደረግ ቅድመ ዝግጅቶች ከወዲሁ መደረግ መጀመራቸውንም ያገኘናቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ያጋሩ