ሪፖርት | ዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ባህር ዳር ላይ እጅ ሰጥተዋል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድቡን ሦስተኛ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3-1 ተሸንፏል።

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ በጀመረበት ቅፅበት ደቡብ አፍሪካዎች ከባድ ጫና ፈጥረው የመጀመሪያዎቹን ቅፅበቶች በኢትዮጵያ ሳጥን ውስጥ ተበራክተው ቢታዩም ዋልያዎቹ አደጋው ወደ ፈጣን ግብነት እንዳይቀየር ተረባርበው አድነውታል። ደቡብ አፍሪካዎች በተመሳሳይ አኳኋን ቅብብሎችን እያቋረጡ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሲታይ ኢትዮጵያዊያኑ እንደሁል ጊዜው በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው በትዕግስት ክፍተቶችን መፈለግን ምርጫቸው አድርገዋል።

እንግዶቹ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ለመፍጠር የሚሞክሩት ጫና ቀስ በቀስ ጋብ እያለ ሲሄድ በተለይም ከሽመለስ በቀለ የሚነሱ ኳሶች ለዋልያዎቹ ጥቃት መነሻነት ፍንጭ ሲሰጡ መታየት ጀምሯል። ያም ቢሆን በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በኢትዮጵያ በኩል ሱራፌል ዳኛቸው ያደረጋቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሁለት ሙከራዎች ሲታዩ ከቆሙ ኳሶች እና ከረጃጅም የእጅ ውርወራዎች ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ የታዩት ደቡብ አፍሪካዊያኑም ለፋሲል ገብረሚካኤል ከባድ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተዋል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የተሻለ መከፈት የጀምረበት እና ሙከራዎች የታዩበት ሆኗል። 26ኛው ደቂቃ ላይም የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተደርጓል። በደቡብ አፍሪካ የቀኝ ሳጥን መግቢያ አካባቢ ረመዳን የሱፍ ከሲድኒ ሞቢ ያስጣለውን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው በድንቅ ሁኔታ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሮን ዌን ዊልያምስ አድኖበታል። ደቡብ አፍሪካዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በሰጡት ምላሽም ታቢሾ ኩቱሜላ ከግራ ወደ መሀል አጥብቦ በመግባት ከግማሽ ጨረቃው ላይ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

ቅብብሎቻቸው ከራሳቸው ሜዳ በመውጣት ባፋና ባፋናዎቹ ደጃፍ መቅረብ የጀመረላቸው ዋልያዎቹ መሀል ለመሀል በተሰነጠቁ ሁለት ኳሶች በድጋሚ ለጎል መቅረብ ችለው ነበር። 37ኛው ደቂቃ ላይ የሱራፌል ድኛቸውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ተከትሎ አንድ ተከላካይ በማለፍ ከግብ ጠባቂው ጋር የተገናኘው አቡበከር ናስር ወደ ግብ የላከውን ኳስ ዊሊያም በማይታመን ቅልጥፍና አድኖበታል። ከደቂቃ በኋላም እንዲሁ አቡበከር ከረመዳን ናስር በደረሰው ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ ገብቶ በዊሊያምስ አናት ላይ ለማስቆጠር የያደረገውን ጥረት ግብ ጠባቂው በድጋሚ አምክኖታል።

በዚህ ሁኔታ ለዕረፍት በተቃረበው ጨዋታ 45ኛ ደቂቃ ላይ ግን ቲቦኖ ሞኮና ወደ ግራ ካጋዳለ የርቀት ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከው የቅጣት ምት ኳስ በፋሲል እጆች መሀል ሾልኮ ሊቆጠር ችሏል። ደቡብ አፍሪካም አጋማሹን 1-0 መምራት ችላለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ዋልያዎቹ ከመጀመሪያው ይልቅ የቅብብል ፍጥነታቸውን ጨምረው በቶሎ ወደ ጎል የመድረስ ፍላጎት ታይቶባቸዋል። የተሻለ ቀጥተኝነት ይስታዋልበት የነበረው ተጋጣሚያቸውም መሪነትን ከማስጠበቅ ይልቅ በተመሳሳይ አኳኋን በፈጣን ጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረቱን ቀጥሏል። የአጋማሸ ቀዳሚ ሙከራ 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ የሱራፌል ዳኛቸው የርቀት ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከባድ ሙከራ ሳያስተናግድ ወደ እንግዶቹ ሜዳ አጋድሎ በቀጠለው ጨዋታ ዋልያዎቹ ያደርጉት የነበረው ጥረት በ67ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ላይ በተሰራ ጥፋት ሳጥኑ መግቢያ ላይ የቅጣት ምት አስገኝቶላቸውል። ቅጣት ምቱን ጌታነህ ከበደ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ በመምታት የዊሊያምስ መረብ ላይ አሳርፏታል። ሆኖም የአቻ ውጤቱ የቆየው ለአምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ደቡብ አፍሪካዎች ከመጀመሪያውም ሲያደርጉት እንደነበረው በረጅሙ ወደ ሳጥን የላኩት የእጅ ውርወራ ተጨራርፎ ከተከላካዮች እያታ ውጪ በነበረው አምበሉ ሞቶቢ ምቫላ አማካይነት ወደ ሁለተኛ ግብነት ተለውጧል።

 

ደቡብ አፍሪካዎች ከሁለተኛው ግብ በኋላም ባገኙት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ሰብረው ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም። 79ኛው ደቂቃ ላይም ተቀያሪው አጥቂ ኤቪደንስ ማጎፓ ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ነበር የተመለሰበት። መስፍን ታፈሰ እና እቤል ያለውን ቀይረው ያስገቡት ዋልያዎቹም ባላቸው አቅም ሁሉ ክፍተቶችን ፍለጋ ገፍተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የቅብብሎቻቸው ጥራት ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ደጋግመው ወደ ባፋና ባፋና ሳጥን የሚያደርሳቸው አልሆነም። ይልቁኑም ለመልሶ ማጥቃት እየተጋለጡ ሄደው በጭማሪ ደቂቃ ሦስትኛ ግብ አስተናግደዋል። ኤቪደንስ ማጎፓ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ለቪክቶር ሌትሶዋሎ አብርዶለት በድጋሚ በመቅበል በፋሲል አናት ላይ ልኮ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በደቡብ አፍሪካ 3-1 አሸናፊት ተጠናቋል።

 

ውጤቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነጥብ ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ ባህር ዳር ስታዲየም ላይ ተሸንፏል። ደቡብ አፍሪካ ነጥቧን ወደ ሰባት ከፍ በማድረግ የማጣሪያውን ምድብ ሰባት መምራት ስትቀጥል ኢትዮጵያ በሦስት ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ለመቅረት ተገዳለች።

ያጋሩ