“ዛሬ ለእኛ ከባድ ቀን እንደነበር ነው የሚሰማኝ” – አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

👉”ሜዳ ላይ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው”

👉”ጎሎቹ የገቡበት ቀላል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል”

👉”የነበሩብንን ክፍተቶች በቶሎ ፈትሸን ከሦስት ቀን በኋላ ለሚደረገው ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጅት እናደርጋለን”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከዛሬው ጨዋታ በኋላ የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው?

“ሜዳ ላይ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው። ከእኛ አጨዋወት ጋር ተያይዞ ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተጭነው ለመጫወት ሲጥሩ ነበር። የእኛን አጨዋወት በጣም ነበር ለማቆም ሲጥሩ የነበረው። ያም ቢሆን ግን በተለይ ከእረፍት በፊት በተወሰነ ደረጃ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን ነበር። ቀድመን ግብ የምናገኝበትንም ያለቀላቸውን ዕድሎች ፈጥረን ነበር። ግን ወደ ግብ መቀየር አልቻልንም። ይህም አንዱ ክፍተታችን ነበር። ግብ ከተቆጠረብን በኋላም ተመልሰን ወደ ጨዋታው አቻ ለመሆን ሞክረናል። ይህ ቢሆንም ግን በተደጋጋሚ በሰራናቸው ስህተቶች ሦስት ግቦችን ማስተናገድ ችለናል። ዛሬ ለእኛ ከባድ ቀን እንደነበረ ነው የሚሰማኝ። እስካሁን ሦስት ጎል ያስተናገድንበት ጨዋታ የለም። ቢሆንም ይህ ውድድር ነው። የነበሩብንን ክፍተቶች በቶሎ ፈትሸን ከሦስት ቀን በኋላ ለሚደረገው ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጅት እናደርጋለን። በአጠቃላይ በተወሰኑ የጨዋታው ደቂቃዎች ላይ በተፈጠሩ ክስተቶች ጨዋታው ከእጃችን መውጣት ችሏል። 

ሜዳ ላይ ስላዩት የቡድናቸው እንቅስቃሴ?
የምናገኛቸውን ኳሶች መጠቀም ብንችል የበለጠ በራስ መተማመናችንን እየጨመርን እነሱ ደግሞ ከፍተው የሚወጧቸውን ቦታዎች በመጠቀም ብዙ ነገሮችን ማድረግ እንችል ነበር። ጎሎች የተቆጠሩብን በቀላሉ ነው። እንደገና መልሰን አቻ መሆን ብንችልም በድጋሜ ጎሎች ገብተውብናል። በተለይ ጎሎቹ የገቡበት ቀላል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል። የነበሩትን ክፍተቶች ማረም ከቻልን መሻሻል እንችላለን ብዬ አስባለሁ። 

ውጤቱ ከሦስት ቀን በኋላ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ ያደረጋል?

ማለፍ ከሆነ ፍላጎታችን ነጥብ እየጣልን ማለፍ እንችላለን ብሎ መናገር ከባድ ነው። ውጤቱ የቀጣዩ ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ዞሮ ዞሮ ቀጣዩ ጨዋታችን ከሜዳችን ውጪ ነው። በዚህም ጨዋታ የምንችለውን አድርገን ወደ ውድድሩ ለመመለስ እንሞክራለን። ይህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ነው። በዚህ ምድብ ውስጥ ያገኘናቸው ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌን ነው። እነዚህ ቡድኖች ደግሞ ከእኛ በደረጃ ከፍ ያሉ ቡድኖች እንደሆኑ ይታወቃል። በዚህ ውስጥ ወደ ውድድሩ ለማለፍ  ከምናደርገው ጨዋታ የምናገኘው ልምድም ጠቀሜታ አለው። በእርግጥ አሁን ከመሪዎቹ ጋር የአራት ነጥብ ልዩነት አለን። እንደ ነጥብ ካሰብከው እዚህ ላይ ሆነን ለማለፍ ማሰብ በጣም ከባድ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ውድድሩ ውስጥ እስካለን የመጨረሻውን ነገር መጠቀም አማራጫችን ነው።